ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማፅናት የብልፅግና ጉዞን ዳር ለማድረስ መረባረብ ይገባል -የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ህዳር 22 ቀን 2015 ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ማፅናትና ለህግ የበላይነት በመገዛት የተጀመሩ የሰላምና ተስፋ ሰጪ የብልፅግና ጉዞን ከዳር ለማድረስ ሁሉም ዜጋ መረባረብ እንዳለበት የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዘሃራ ዑመድ ተናገሩ።

ምክትል አፈ-ጉባኤዋ ዛሬ በድሬዳዋ በተከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አከባበር ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሚፈለገው ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ዕውን የሚሆነው ሁሉም ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ተገዥ ሲሆን ነው ብለዋል።

የደመቀው ብዝሃነታችንና የተጋመደው ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማፅናት ለዘላቂ ሰላምና ልማት ቀጣይነት መረጋገጥ መረባረብ የዜጎች ሁሉ ኃላፊነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሁሉም በየተሰማራበት መስክ ለሀገር ታላቅነት ሌት ተቀን በመረባረብ ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

ምክትል አፈ-ጉባኤዋ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህግ የበላይነትን በማክበር እና በማስከበር አርአያ መሆን እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈትሂያ አደን በበኩላቸው፤ ቀኑ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያፀኑና በሀገር መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት በሚፈጥሩ ዝግጅቶች በአስተዳደሩ ገጠር እና ከተማ ቀደም ሲል ሲከበር መቆየቱን አውስተዋል።

የዛሬው የማጠቃለያ መርሃ-ግብር የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በፀና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ዳር ለማድረስና በህገ-መንግሥቱ የተጎናፀፍናቸውን መብቶች ለመጠበቅ ቃላችንን የምናድስበት ነው ብለዋል።

ቀኑ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ብስለት በተሞላበት የሰላም ዲፕሎማሲ መግባባት ላይ በተደረሰበት ወቅት ላይ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ናቸው።

ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በተገቢው መንገድ መያዝና ዕውን ማድረግ ለኢትዮጵያውያን የቅንጦት ሳይሆን የሀገር ሰላም፣ አንድነት፣ ሉአላዊነት፣ ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ቀኑን የተመለከተ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የአዲስ አበባ አስተዳደርና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ዑጋዞች፣ አባገዳዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም