በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለደቡብ ሱዳን ተማሪዎች 6 ሺህ የመማሪያ መጽሐፍቶችን አበረከቱ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለደቡብ ሱዳን ተማሪዎች 6 ሺህ የመማሪያ መጽሐፍቶችን አበረከቱ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 22/2015 በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለደቡብ ሱዳን ተማሪዎች 6ሺህ የመማሪያ መጽሐፍት ድጋፍ አበረከቱ።
ድጋፉን በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የንግድ ማህበረሰብ ከደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር መሆኑ ተገልጿል።
ድጋፉ ለ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚያገለግል 6ሺህ የሂሳብና ሳይንስ መማሪያ መጽሐፍት መሆኑም ተገልጿል።
የመጽሐፍቱ ልገሳ በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሀገሪቱ እያበረከቱ ከሚገኙት የማህበራዊ ሃላፊነት ተግባራት መካከል አንዱ እንደሆነም ተመላክቷል።
በደቡብ ሱዳን የተለያዩ ኩባንያዎች ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያውያኑ በሀገሪቱ የስራ እድል ፈጠራ፣ ልምድ ልውውጥ፣ እንዲሁም ቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም ተገልጿል።
መሰል ድጋፎችን በቀጣይ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል መህዲ፣ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም ከደቡብ ሱዳን የትምህርት ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ ለመጽሐፍቱ ልገሳ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ኩባንያዎች እና ግለሰቦች የምስጋናና የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።