ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የተጓተቱ ግዙፍ የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለልማት እንዲውሉ ይሰራል - የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር እንጂነር አይሻ መሐመድ

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 22/2015 በአማራ ክልል በተለያየ ምክንያት የተጓተቱ ግዙፍ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለልማት እንዲውሉ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የድጋፍ፣ የክትትልና የቁጥጥር ስራ ይሰራል ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ አስታወቁ።

በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ ግዙፍ የመስኖ ልማት ግድብ ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ግምገማ ትናንት በባህር ዳር ተካሂዷል።

በግምገማው ለፕሮጀክቶቹ መጓተት የተቋራጮች፣ ዲዛይነሮችና አማካሪዎች አቅም ማነስ እንዲሁም የተጋነነ የካሳ ጥያቄዎች በምክንያትነት ተነስተዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቶቹ የቆዩና ጊዜ የተፈራረቀባቸው መሆናቸው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ሚኒስትር እንጂነር አይሻ መሐመድ በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።

በመሆኑም በፕሮጀክቶቹ ያጋጠሙ ችግሮችን በተቀናጀ አግባብ በመፍታት ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ሚኒስቴሩ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል ብዋል።

የተቋራጮችንና የአማካሪዎችን አቅም ከማጎልበት ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመናበብና በመቀናጀት በቀናነት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለረጅም ዓመታት የተጓተቱ ግዙፍ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በክልሉም ሆነ በሀገር ሃብት ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ናቸው።

የፕሮጀክቶች መጓተት የመልካም አስተዳደር ችግር ጭምር መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተለይም ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ተገቢ ባልሆነ መንገድ የሚቀርበው ጥያቄ እልባት ማግኘት አለበት ብለዋል።

አርሶ አደሩ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት የካሳ ክፍያ እንደሚከፈለው ጠቅሰው፤ ከዚህ ውጭ የሚደረግ ድርጊት ልማትን የሚጻረር ተግባር በመሆኑ በየደረጃው ያለ አመራር ማስቆም እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ ሁሉም በባለቤትነት የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው ገልጸው፤ የክልሉ መንግሥት ተገቢውን ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

የርብ ግድብንና መገጭ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክትን በተቋራጭነት እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የውሃ ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ በእምነት ጋሸው እንዳሉት ስራውን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ አግባብ ያልሆኑ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል።

ስለሆነም መንግሥት የካሳ ክፍያ ሥርዓቱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ለስራው እንቅፋት እንዳይሆን በሚያስችል ሁኔታ አሰራር ሊዘረጋለት እንደሚገባ ጠይቀዋል።

በክልሉ እየተገነቡ ከሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል የላይኛው እና የታችኛው ርብ መስኖ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም የመገጭና ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ።

በመድረኩ የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ 600 የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ለአማራ ክልል መንግሥት አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም