ቀጥታ፡

የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ -የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 22/2015  የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ ጊዜ  በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ31ኛ ጊዜ  በድሬዳዋ ከተማ ይከበራል።

ቀኑ "አካታች የፈጠራ ሥራና ሽግግራዊ መፍትሔ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተደራሽነት" በሚል መሪ ቃል ነገና ከነገ በስቲያ እንደሚከበር ተገልጿል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ቀኑን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ሚኒስቴሩ የአካል ጉዳተኞች መብትና ጥቅም እስከሚረጋገጥ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል።

የዘንድሮ በዓልም በአካል ጉዳተኞች ላይ ያለውን አገራዊ ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ መብትና ጥቅሞቻቸው እንዲረጋገጥ የሚያግዝ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተለይም በአካል ጉዳተኞች ላይ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶችን ለመቀየር የተጀመሩ ሥራዎች እንዲጠናከሩ ያደርጋልም ብለዋል።

ሚኒስትሯ ሕብረተሰቡ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ የራሱ ጉዳይ በማድረግ መንቀሳቀስ  እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የአካል ጉዳተኞች ቀን  በሚከበርበት ወቅት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡበት ጉዳዮች ላይ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች  ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፤ የበዓሉ መከበር አካል ጉዳተኞች በጋራ  ድምጻቸውን ለማሰማት ዕድሉን ያገኛሉ ብለዋል ።

ሚኒስቴሩ አካል ጉዳተኞች በሁሉም የልማት መስኮች እኩል ዕድል አግኝተው ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑና የፌዴሬሽኑን አቅም ለማጎልበት እያደረገ ላለው ጥረት አመስግነዋል።

በቀጣይም አካል ጉዳተኞች በሁሉም መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ  እንዲሆኑ ሰው  ሰራሽ የአካል ድጋፎችን የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም