በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን መቋቋሙ ባለሃብቶች ከአምራችና ላኪነት ባሻገር በአገልግሎት ዘርፍ እንዲሰማሩ ሰፊ እድል ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን መቋቋሙ ባለሃብቶች ከአምራችና ላኪነት ባሻገር በአገልግሎት ዘርፍ እንዲሰማሩ ሰፊ እድል ይፈጥራል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 22/2015 በኢትዮጵያ የሚቋቋመው ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሃብቶች ከአምራችና ላኪነት ባሻገር በአገልግሎት ዘርፍ እንዲሰማሩ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የሕግና ፖሊሲ አማካሪ ዶክተር ሐብታሙ ስማቸው፤ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን በሚፈጥሩ ፖሊሲዎች እና ንግድን በሚያሳልጡ አቅርቦቶች የተደገፈ መሆኑን ገለጸዋል።
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን፣ የሎጂስቲክስ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፓርኮችን፣ የአገልግሎት እና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎችን ያቀፈ ነው፡፡
ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በሚፈጥሩ ፖሊሲዎች፣ ንግድን በሚያሳልጡ አቅርቦቶች፣ መሰረተ-ልማቶች እና አገልግሎቶች የተደገፈ እንዲሁም የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና ልዩ ማበረታቻዎችን የያዘ ነው።
በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚጠራ ሥፍራ ባይኖርም፤ በዘርፉ ሊመደቡ የሚችሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ነፃ የንግድ ቀጣናዎች ባለቤት መሆኗ ይታወቃል።
ዶክተር ሐብታሙ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የሚሰማሩ ባለሃብቶች በአምራችነትና በላኪነት የሥራ ዘርፍ ብቻ የተወሰኑ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ይህ ደግሞ ከአምራችነትና ከላኪነት ባሻገር ያሉ የአገልግሎት ዘርፎችን በመገደብ እንደ አገር የሚገኘውን ጥቅም ውስን አድርጎት ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
ይህን መነሻ በማድረግም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፓርክ፣ የሎጂስቲክስ ፓርኮችንና የአገልግሎት ዞኖችን ለማካተት ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማቋቋም ማስፈለጉን ተናግረዋል።
ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የተገኙ ልምዶች እንደሚያሳዩት፤ ፓርኮች በባህሪያቸው ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሥፍራዎች በመሆናቸው አሰራራቸውን ማስፋት በማስፈለጉም እንዲሁ።
የሚቋቋሙት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ሁሉንም የኢንቨስትመንት አገልግሎቶች በተቀላጠፈ ሁኔታ በአንድ ማዕከል መስጠት የሚያስችሉ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ማዕከሉ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተቆጣጣሪነት የሚተዳደር እንደሚሆንም ተናግረዋል።
የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች መቋቋም ከመንግሥት ባሻገር የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ሐብታሙ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጥሬ እቃዎችን እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ በመላክም ለውጭ ምንዛሪ ግኝትም አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ማምረት የሚችሉ ፋብሪካዎች በኢንቨስትመንት መስኩ እንዲሰማሩ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በሚቋቋመው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በተለያዩ ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ያሉት ሲሆን ለአብነትም የገቢ ግብር እፎይታ አንዱ መሆኑንም አንስተዋል።
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ማቋቋም ለዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር ተጨማሪ ምርትና አገልግሎት እንዲኖር ያስችላሉ፡፡
ኢትዮጵያም የአፍሪካ የነፃ የንግድ ቀጣና አባል እንደመሆኗ መጠን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማቋቋሟ ከቀጣናው ገበያ የሚገባትን እንድታገኝ ያስችላታል፡፡
ኢትዮጵያ ያለችበት ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ ለንግድ ትስስር አመቺነት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ተግባራዊ የሚደረግበትና የሚመራበት የሕግ ረቂቅ እየተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ከአፍሪካ አገራት ጋና፣ ሞሪሽየስ፣ ሴኔጋል እንዲሁም ሌሎች ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አቋቁመው በመሥራታቸው በዘርፉ ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡ አገራት መካከል መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡