ቀጥታ፡

በወረዳው 600 ቤተሰቦችን የመብራት ሃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ሀዋሳ ህዳር 21/2015 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ 600 አባወራና እማወራዎችን የመብራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ከፀሐይ ብርሃን የሚገኝ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሡልጣን ወሊ እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ ለነዋሪዎች ሁለንተናዊ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ፕሮጀክቱ በሸበዲኖ ወረዳ ሌልቾ ቀበሌ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለመብራትና ለምግብ ማብሰያ እንዲሁም ለግብርና ምርታማነት ጥቅም ላይ ማዋልን ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫ ማድረጉን ገልጸዋል።

በአገር ደረጃ "ተደራሽ ታዳሽ ኃይል ለግብርና ምርታማነት" የተሰኘ መርሀ ግብር ተቀርፆ በአራት ክልሎች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዚህም ከሰባት ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦቱ ተጠቃሚ የሚሆኑ ቤተሰቦች የመስኖ ልማት ማከናወን የሚችሉበት ዕድል እንደሚፈጥርላቸውም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚደረግባቸው አካባቢዎች በአጠቃላይ 1 ሺህ 325 ሄክታር መሬት በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የውሀ መሳቢያዎችን በመጠቀም የመስኖ ልማት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በሲዳማ ክልል የሸበዲኖ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አጋና ኔቶ በወረዳው የኤሌቾ ቀበሌ በፀሐይ ብርሃን የሚሰራ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያገኝበት ፕሮጀክት ይፋ መሆኑ የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ታዳሽ ኃይሉን በፀኃይ ብርሀን ኃይል ለሚሰሩ የውሀ መሳቢያዎች በማዋልና የመስኖን ልማትን በማስፋፋት  320 ሄክታር በላይ እንደሚያለማ አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የወረዳው አስተዳደር አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር በየነ ሀሪሶ ፕሮጀክቱ ለአካባቢያችን ብርሀን ይዞ ከመምጣቱም ባሻገር የግብርና ልማታችንን የሚያቀላጥፍልን በመሆኑ እጅግ ተደስተናል ብለዋል፡፡

የተሻሻሉ የአቦካዶ ዝርያ ተክሎችንና ሌሎች ምርቶችን በመስኖ በማልማት እንደሚተዳደሩ የተናገሩት አርሶ አደሩ፤ ለውሀ መሳቢያ ማሽን የሚሆን ነዳጅ ለማግኘት ሲቸገሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ይህንን ችግራቸውን እንደሚፈታላቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም