የውጭ ባለ ሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ባለ ሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 22/2015 በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የውጭ ባለ ሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮችና የኢኮኖሚና ንግድ አታሼዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዕድሎችና የኮሚሽኑ የአንድ ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያውም ባለሃብቶች አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኪሚሸነር ለሊሴ ነሜ መድረኩ በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማስተዋወቅና ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች ለማስረዳት መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ዙሪያም ማብራሪያ መሰጠቱን ጠቅሰው ለኢንቨስትሮች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የ6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የውጪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ዕቅድ መያዙን የገለጹት ኮሚሽነሯ ለዚህም መድረኩ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ አሁን እየተፈጠረ ያለው ሰላም፣ የኢንቨስትመንት አዋጅና ደንቡ መሻሻልና ሌሎችም ዘርፉን ይበልጥ ምቹና ተመራጭ እያደረገው መሆኑን ገልጸዋል።
በሪፎርም ሂደታቸው ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ማሳለጣቸውና ክልሎችም ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ዝግጁ መሆናቸው ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የሚረዱ ናቸው ብለዋል፡፡
ለአምባሳደሮች፣ ለኢኮኖሚና ንግድ አታሼዎች በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች በኮሚሽኑ ከፍተኛ የህግ አማካሪ ዶክተር ሃብታሙ ስማቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢንቨስተሮች ሊሳተፉ የሚችሉባቸው ከአምስት በላይ መስኮች መለየታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በማብራሪያው ላይ የተገኙት ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ሰፊና አማራጭ የኢንቨስትመንት መስኮች መኖራቸውን ተረድተናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ እምቅ ሃብትና ሰፊ የመልማት እድል ያላት አገር ስለመሆኗም ተገንዝበናል ነው ያሉት።
ምባሳደሮቹ ፣የኢኮኖሚና ንግድ አታሼዎች በኢትዮጵያ በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድልና አማራጮችን በመመልከት እንዲያለሙ ጥሪ ቀርቧል፡፡