ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ተቋምን በሰው ኃይል፣ በዘመናዊ አሰራርና በአገር በቀል ቴክኖሎጂ እየገነባች ነው

200

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ተቋምን በሰው ኃይል፣ በዘመናዊ አሰራርና በአገር በቀል ቴክኖሎጂ እየገነባች መሆኑን የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አሰተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ተናገሩ።

በዓለም አቀፉ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባዔ ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ያላትን ልምድ ማካፈሏን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በጉባዔው ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን መረብ አስተዳደር እያከናወነች ያለውን ተግባር በማካፈል ከሌሎችም ልምድ እየወሰደች መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዓለም አቀፉ ጉባዔ አገራት የተሞክሮና ልምድ ልውውጥ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የዓለም የትስስር መድረክና ትልቅ ሃብት የሆነው ኢንተርኔት ደኅንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ እንዲሆን አገራት በጋራ እንደሚሰሩ የገለጹ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በጉባዔው ያላትን ልምድ አጋርታለች ብለዋል።

የሳይበር ደኅንነት፣ የፖሊሲ ጉዳይ፣ በመመሪያና በቁጥጥሮች ላይ ያሉ አሰራሮች  ተግባራዊ ሲደረጉ በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ውይይት መደረጉንም አንስተዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ልምዱን አጋርቷል ብለዋል።

በሳይበር ደኅንነት አስተዳደር መመሪያና ፖሊሲዎች ላይ ከሌሎች አገሮች የተነሱ ጉዳዮችንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በበይነ-መረብ አማካኝነት እንዲያከናውኑ ለማስቻል የ2025 ዲጂታል ስትራቴጂ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሰረታዊ በሆኑ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትና የሳይበር ደኅንነት ማስጠበቅ ላይ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሳይበር ደኅንነትን አጀንዳ በማድረግ ለሌሎች አገሮች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሥራ እያከናወነች በመሆኑ ያለፈችበትን ልምድ ለማካፈልም ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ጠንካራ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ተቋምን በሰው ኃይል፣ በዘመናዊ አሰራርና በአገር በቀል ቴክኖሎጂ እየገነባች ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባዔ ኢትዮጵያ የዘርፉን ተሞክሮዋን ከማጋራት ባለፈ ራሷን እያስተዋወቀች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ጉባዔው በበይነ-መረብ አስተዳደር፣ በኢንተርኔት ተደራሽነት፣ በመሰረተ-ልማት፣ በሳይበር ደኅንነትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም