የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኦሪገኑ 18ተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውጤት ላመጡ አትሌቶች የመሬት ካርታ አስረከበ

219

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኦሪገኑ 18ተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውጤት ላመጡ አትሌቶች የመሬት ካርታ አስረከበ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ውጤት ላመጡ አትሌቶች ቃል የተገባውን የመሬት ካርታ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ አስረክበዋል፡፡

ከንቲባዋ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የአትሌቲክሱን ዘርፍ መልሶ በማነቃቃት ረገድ የፌዴሬሽኑና የአትሌቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ በኦሪጎኑ የዓለም ሻምፒዎና የመጣው ውጤት ከተማ መስተዳድሩ በህፃናትና ታዳጊዎች ስፖርት ላይ እየሰራ ላለው ሥራ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል።

በመሆኑም ከተማ መስተዳድሩ በኦሪጎኑ የዓለም ሻምፒዮና ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች እንደየደረጃቸው  የመሬት ካርታ ማስረከቡን ተናግረዋል።

በቀጣይም አትሌቲክሱን ለመደገፍ የተጀመሩ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ግንባታዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የከተማ አስተዳደሩ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በቅንጀት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ ከተማ መስተዳደሩ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርባ፤ ይህም አትሌቶች በቀጣይ ለሚኖራቸው ውድድር መነሳሳትን ይፈጥራል ብላለች፡፡

የአትሌቲክስ የልህቀት ማዕከል ባለመኖሩ ምክንያት አትሌቶች በየሆቴሉ በመሆን ልምምድ እንደሚሰሩም ነው የገለጸችው፡፡

ከዚህ አኳያ የከተማ አስተዳደሩ አትሌቶችን በአንድ ለማሰባሰብ የሚያስችለውን የአትሌቲክስ የልህቀት ማዕከል ግንባታ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቃለች፡፡

የከተማ መስተዳደሩ በበኩሉ የአትሌቲክስ የልህቀት ማዕከል ግንባታ በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ  አፅንኦት ሰጥቶ እንደሚመለከተው ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም