በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ እያጋጠመ ያለውን የኢንተርኔት መቆራረጥ ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል

152

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 በዓለም አቀፉ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ እያጋጠመ ያለውን የኢንተርኔት መቆራረጥ ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ የ17ተኛው የኢንተርኔት ጉባኤ ተሳታፊዎችና ፓናሊስቶች ገለጹ።

በአዲስ አበባ የሚካሄደው 17ተኛው የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ በ3ተኛው ቀን ውሎው ''በኢንተርኔት መቆራረጥና የኔትወርክ ፖሊሲ ''እንዲሁም 'የኢንተርኔት መቆራረጥን በዘላቂነት መከላከል'' በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መክሯል።

በመድረኩም የኢንተርኔት መቆራረጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያጋጥም የሚችል ቴክኒካዊ ሂደት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ውይይቱን የመሩት የዓለም አቀፍ የዲጂታል ትብብር አባል ሺታል ኩማር በዚሁ ወቅት የኢንተርኔት መቆራረጥ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

የኢንተርኔት ተደራሽነት በዓለም አቀፍ የዲጂታል ግንባታ ውስጥ ሚናው የጎላ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት የኢንተርኔት መቆራረጥን በዘላቂነት ለመቅረፍ በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

እንዲሁም ከኢንተርኔት አገልግሎት ውጭ ያሉ ማህበረሰቦችን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ለኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ዘላቂና ቀጣይነት ያለው አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ መንግስት፣ የሲቪል ማህበረሰብና የዘርፉ ተዋንያን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው በጋራ መስራት እንደሚገባቸው አብራርተዋል።

በኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ የባለድርሻ አካላት አማካሪና የዲጂታል ዘርፍ አባል ቡርና ማርቲኒስ በተለያዩ ሀገራት የኢንተርኔት መቆራረጥ እንደሚያጋጥም በማንሳት፤ ፖሊሲ አውጪዎች፣ መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የኢንተርኔት መቆራረጥን ለማስቀረት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የባህርዳር ዩንቨርሲቲ መምህርና የዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ግርማ አሸብር እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የስልክ አገልግሎት በአግባቡ ያልተዳረሰበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከመድረኩ ከሚገኘው ግብዓት ኢትዮጵያም ተጠቃሚ እንደምትሆን መግለጻቸውን አስታውሰው፤ ይህም በኢትዮጵያ ያላውን ተደራሽነት በማስፋት ረገድ ጉልህ ሚና እንሚኖረው ተናግረዋል፡፡

መድረኩ ኢትዮጵያ በጀመረችው የዲጂታል ግንባታ ዘርፍ ብዙ ስራዎች እንደሚጠብቋት ያመላከተ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም