የፌደራል ፖሊስ የአክሱም ጽዮን ማርያም ክብረ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የአክሱም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ምስጋና አቀረበ

224

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የአክሱም ጽዮን ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የአክሱም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ምስጋና አቀረበ።

ዓመታዊው የአክሱም ጽዮን ማርያም ክብረ በዓል በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የአክሱምና አድዋ ጸጥታ ዘርፍ አዛዥ ኮማንደር ጌትነት ከበደ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ፖሊስ በዓሉን በሰላም ለማክበር ቀደም ብሎ  ከሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በዓሉ በሰላም እንዲከበር የፌደራል ፖሊስና የአካባቢው ማህበረሰብ በጋራ መስራታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የአክሱም ጽዮን ማርያም ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር ከጸጥታ ኃይሎች በተጨማሪ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ከፍተኛ ሚና ማበርከታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የእምነቱ ተከታዮች ወደ ቤተክርስቲያን በመምጣት በዓሉን በደመቀ ሁኔታ በሰላም አክብረዋል ብለዋል፡፡

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የአክሱም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም