ቀጥታ፡

"የተጀመረው አዲስ የለውጥ ሂደት አሸናፊ ሆኖ ይወጣል" - የብአዴን ሊቀመንበር

አዲስ አበባ መስከረም 17/2011 በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተጀመረው የለውጥ ትግል ውስጥ  የተከሰቱ ችግሮችን በማለፍ "አዲሱ መንገድ አሸናፊ ሆኖ መውጣቱ እርግጥ ነው" ሲሉ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሊቀ መንበር ገለፁ። ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው 12ኛ የብአዴን ድርጅታዊ ጉባኤ "የለውጡ ቀጣይነት ለአማራ ህዝቦች ተጠቃሚነትና ዲሞክራሲያዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከናወነ ይገኛል። ሊቀመንበሩ አቶ ደመቀ መኮንን የብአዴን 12ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ያጋጠሙ ፈተናዎች ከአሮጌው መንገድ ለመላቀቅና አዲሱን ለመገንባት በሚደረግ ትግል የተከሰቱ ናቸው። አቶ ደመቀ በዚሁ ንግግራቸው፤ ችግሮቹ "በአሮጌውና በአዲሱ መካከል በተፈጠረ ቅራኔ የተወለዱ ናቸው፤ ያም ሆኖ ግን በሂደቱ የአዲሱ መንገድ አሸናፊ እንደሚሆን በእርግጠኝነት እነግራችኋለሁ" ብለዋል። ይህ እንዲሆን ግን ህዝቡ በለውጡ የሚፈልገውን ዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ነፃነትና እኩልነትን ለማሳካት ይቻል ዘንድ "መወጋገዙን ትተን መተጋገዝ፣ መጠላለፉን ትተን  መተቃቀፍን፣  መሰባበሩን ትተን መተባበርን መጀመር አለበን" ሲሉም አሳስበዋል። በበርካታ ትግልና መስዋዕትነት እውን እየሆነ ባለው ዴሞክራሲያዊ መድረክና የለውጥ ጉዞ ጥሪ ተደርጎላቸው ወደአገር ቤት የመጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ጉዟቸውን ወደፊት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው የገለጹት። "ወደፊት መውደቅም መንገድ መቀነስ ነው" የሚል አገራዊ አባባልን የጠቀሱት አቶ ደመቀ፤ ትርፍ የሚገኘው ወደፊት በመጓዝ በመሆኑ መድረኩን የሚመጥን ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የሁሉም ኃብት እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል። በዚህ ረገድ በ38 ዓመታት ጉዞ በርካታ የትግል ተሞክሮ የቀመረው ብአዴን ዝግጁ መሆኑን ነው ያረጋገጡት። ድርጅቱ ለመላው የአማራ እና የኢትዮጵያ ህዝብ  የትግል መነሻ መሆኑን አውስተው፤ ክፉውንም ደጉንም በትግስትና በአስተዋይነት በጥበብ በማለፍ "ለአሁኑ የለውጥ ተስፋ የበቃ አንጋፋ ድርጅት" ብለዋል። አሁን ለመጣው የሰላም፣ የይቅርታና የፍቅር እንዲሁም የነፃነት ተስፋ መለምለም ብአዴን የተጫወተው ሚና ጉልህ እንደሆነም ገልፀዋል። "ይህችን ገናና አገር ወደ ክብሯ ለመመለስ፣ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ጋር ትግል በመጀመራችን የተስፋ ፍንጣቂዎችን ለማየት ጀምረናል" ያሉት የብአዴን ሊቀ መንበር፤ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ "በስኬታችን ውስጥ ድክመቶች በማሳየታችን ህዝባችንን ቅር አሰኝተን ግጭት ውስጥ ገብተናል፤ ግጭቶቹም ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል" ብለዋል። አሁን ደግሞ በህዝቡ ውስጥ ቅሬታ ከፈጠሩትና ወደ ግጭት ካስገቡት ችግሮች ለመላቀቅ "ባደረግነው ትግል ተስፋ ያዘለ ለውጥ ማየትም ጀምረናል" ሲሉ ገልጸዋል። የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በከፍተኛ መስዋእትነት የመጣ፣ ወደፊትም ብርቱ ጽናትንና ትግልን የሚጠይቅ መሆኑን አቶ ደመቀ አስገንዘበዋል። "ለውጡ የጎደለንን የምንሞላበት፣ ያረጀውን የምናድስበት፣ ያዘመመውን የምናቃናበት፣ የጀመርነውን ዳር የምናደረሰበት ስር ነቀል ለውጥ ነው" ብለዋል። በሰለጠነ ዘመን የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከኃይል አስገዳጅነት ይልቅ በሀሳብ ልዕልና አስረጅና አሳማኝ የማድረግን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጠውታል። "ለዚህ ትውልድ የአርበኝነት ብያኔ ድህነትን ከልብ መጠየፍና በልማት ድል መንሳት ነው፤ በዚህ  የለውጥ ዘመን አርበኝነት ጥላቻን በፍቅር፣ ቂም በቀልን በይቅርታ፤ መከፋፈልና መናቆርን በመቻቻልና በመደመር መሻገር ነው" ብለዋል። አሁን የተደረሰበት ምእራፍ ከብዙ ጉዞ በኋላ የመጣ መሆኑን ያወሱት ሊቀ መንበሩ፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በሁለት ፅንፈኛ ኃይሎች በተወጠረ ፖለቲካ ውስጥ እንደመትገኝ ጠቅሰዋል። "በአንድ በኩል ሁሉን የደፈጠጠና የጠቀለለ አገራዊ ማንነትን ብቻ አንግቦ የተነሳ የጠቅላይና አሀዳዊ አመለካከት የኢትዮጵያን መልከ ብዙ እውነታ በካደ መልኩ ፅንፈ ይዞ  እየተራገበ የሚጓዝ  ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ብሄረሰባዊ ማንነትነ ከሌሎች መነጠያነትና ማግለያ ያደረገና ፅንፈኛ ብሄርተኝነት የሚቀነቀንበት ነው" ብለዋል። ብአዴን በእነዚህ ሁለት ፅንፎች መካከል ሚዛን  ሆኖ የሚቆም ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት የሚጠይቅ ወቅት ላይ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት። "የምንሮጠው ሩጫ ከችግሮቻችን አቅም በላይ መሆን አለበት" ያሉት አቶ ደመቀ፤ ህዝቡ ተስፋ ሳይቆርጥ በትእግስት ጊዜ መስጠቱን አመልክተዋል። ድርጅቱ የህዘቡን ጥያቄ ለመመለሰ የሚመጥን አዳዲሰ አመራር አባላትን ማምጣት እንደሚጠይቀው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም