ስቴፋኒ ፍራፓርት - በፊፋ ዓለም ዋንጫ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ዋና ዳኛ

144

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21 ቀን 2015 በኳታር አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የተለዩ ገጽታዎች ያሉት ነው ማለት ይቻላል።

ከፍተኛ ወጪ የወጣበት የዓለም ዋንጫ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ በበጋ ወቅትና በአረቡ ዓለም የተካሄደ መሆኑ ለየት ያደርገዋል።

የዘንድሮው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ዳኞች እንዲያጫውቱ የተመረጡበትም ነው።

ሳላማ ሙካንሳንጋ ከሩዋንዳ፣ ዮሺሚ ያሚሺታ ከጃፓን እና ስቴፋኒ ፍራፓርት ከፈረንሳይ በዓለም ዋንጫው እንዲያጫውቱ የተመረጡ ሴት ዳኞች ናቸው።

ከተመረጡት ዳኞች መካከል የ38 ዓመቷ ፈረንሳዊት ስቴፋኒ ፍራፓርት ነገ ከምሽቱ 4 ሰዓት በአል በይት ስታዲየም ጀርመን ከኮስታሪካ የሚያደርጉትን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት እንደምትመራ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) አስታውቋል።

ይህም ፍራፓርትን በፊፋ ዓለም ዋንጫ ታሪክ በዋና ዳኝነት የምትመራ የመጀመሪያ ሴት ያደርጋታል።

በምድብ ሶስት ፖላንድ ከሜክሲኮ ያለ ምንም ግብ አቻ ሲለያዩ አራተኛ ዳኛ በመሆን በፊፋ ዓለም ዋንጫ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ዳኛ በመሆን አዲስ ታሪክ ሰርታለች።

ፍራፓርት እ.አ.አ 2021 የፊፋ ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ የመራች የመጀመሪያ ሴት ዋና ዳኛ እንደነበረች አይዘነጋም።

በወቅቱ በመሐል ዳኝነት የመራችው የኔዘርላንድስና የላቲቪያን ጨዋታ ነበር።

በተጨማሪም በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና በፈረንሳይ ሊግ 1 ጨዋታዎችን የመራች የመጀመሪያ ሴት ዋና ዳኛም ናት ስቴፋኒ ፍራፓርት።

ፈረንሳዊቷ ዳኛ እ.አ.አ ከ2009 አንስቶ በፊፋ ስር ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች።

ነገ በሚደረገው የጀርመን እና ኮስታሪካ ጨዋታ ብራዚላዊቷ ኔውዛ ባክ እና ሜክሲኳዊቷ ካረን ዲያዝ መዲና የፍራፓርት ረዳቶች ናቸው።

ይህም የሁለቱን አገራት ጨዋታ በፊፋ ዓለም ዋንጫ ታሪክ ሁሉም ሴት ዳኞች የመሩት የመጀመሪያ ጨዋታ ይሆናል።

ዓለም አቀፉ የስፖርት ታሪክና ስታስቲክስ ፌዴሬሽን ስቴፋኒ ፍራፓርትን እ.አ.አ በ2019፣ 2020 እና 2021 ምርጥ ሴት ዳኛ በሚል ሽልማት አበርክቶላታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም