ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ልማት የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት በሙሉ አቅማችን እንደግፋለን--የዲፌንድ ኢትዮጵያ ዩኬ ግብረ-ሃይል አስታወቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21 ቀን 2015 የዲፌንድ ኢትዮጵያ ዩኬ ግብረ-ሃይል አባላት በመንግስትና በህወሓት መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወቱ ገለጸ።

የግብረ ሀይሉ አባላት ይህን ሁለተኛ አመት የምስረታ በአላቸውን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባከበሩበት ወቅት ለኢትዮጵያ ልማት የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት በሙሉ አቅማችን እንደግፋለን ብለዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት ሁለት አመታት ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ የውጪ ሀይሎች ከፍተኛ ጫና ለመፍጠር ያደረጉትን የተቀናጀ ጥረት ለመቋቋም በዩናይትድ ኪንግደምና አየር ላንድ በሚኖሩ ኢትዮጰያውያንና ትውልደ ኢትዮጰያውያን አማካይነት 'ኢትዮጵያን እንታደግ' በሚል ግብረ-ሀይሉ መመስረቱን አስታውሰዋል፡፡

ግብረ-ሃይሉ ለኢትዮጰያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ቤተሰቦችና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የበኩሉን ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በነበረችበት ወቅት በዲፕሎማሲ፣ በሚዲያ ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂና በሎቢንግ ራሱን በማደራጀትና ከሌሎች የኢትዮጰያ ኮሚኒቲዎች ጋር በመተባበር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ አዎንታዊ ሚና ሲጫወት መቆየቱን አስታውሰዋል።

በተፈረመው የሰላም ስምምነት ዙሪያም ለግብረ ሀይሉ አባላት ሰፊ ማብራሪያ አቅርበው፣ የሰላም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን አባላቱ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል፡፡

አባላቱ ዘላቂ ሀገራዊ ጥቅሞችን ለማረጋገጥ የጀመሯቸውን የገጽታ ግንባታ፣ የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም እንዲሁም ለኢትዮጰያ ምርቶች ገበያ የማፈላለግ ስራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የግብረ ሀይሉ አባላት ላደረጉት አስተዋጽኦም አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዲፌንድ ኢትዮጵያ ዩኬ ግብረ-ሃይል አስተባባሪ አቶ ዘላለም ተሰማ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ መሰረት የሚጥል ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ችግር ውስጥም ሆና በርካታ የልማት ስራዎችን ስታከናውን እንደቆየች በማስታወስ የሰላም ስምምነቱ የልማት ስራዎቹን ይበልጥ ለማከናወን እድል የሚሰጥ በመሆኑ ለልማት በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የግብረ ሃይሉ አባላት ሙሉ አቅማቸውን ያውላሉ ብለዋል፡፡

በእለቱ ለግብረ ሀይሉ አባላት የምስጋና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ስነ-ስርአት መካሄዱን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

ዲፌንድ ኢትዮጵያ ታስክፎርስ ኢሮፕ’ የተሰኘው ጥምረት ከሁለት ዓመት በፊት የተመሰረተ ሲሆን ጥምረቱ በቤልጂየም፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ስዊዘርላንድ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ጣልያን፣ ስዊድን፣ ኔዘርላንድስ፣ ኖርዌይ፣ ስፔንና ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የሚያስተባበር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም