ቀጥታ፡

ዲጂታል ዲፕሎማሲውን በመጠቀም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ እናስተዋውቃለን- ዲፕሎማቶች

ጎንደር (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 ዲጂታል ዲፕሎማሲውን በመጠቀም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ፀጋዎች ለሌላው አለም በማስተዋወቅ የጎብኚዎችን ፍሰት ለማሳደግ በትኩረት እንሰራለን ሲሉ በውጭ ሀገራት ተመድበው የሚሰሩ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ተናገሩ፡፡

ዲፕሎማቶቹ በጎንደርና አካባቢው የሚገኙ ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ጉብኝተዋል።

በህንድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት በመሆን የሚሰሩት ይበልጣል ተገኘ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤  አለም ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ መሸጋገሩ ልማዳዊውን የዲፕሎማሲ አሰራር ወደ አዲስ የዲጂታል ዲፕሎማሲ እንዲቀየር ማስገደዱን ገልጸዋል።

ዲጂታል ዲፕሎማሲው የኢትዮጵያን የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዘርፉን በማስተዋወቅ ለአለም ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች በአለም አቀፍ ደረጃ በስፋት በማስተዋወቅ የጎብኚዎችን ፍሰት ለመጨመርም ሆነ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ለማሳደግ አበክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ካውንስለር ሱልጣን ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች ባለቤት ብትሆንም የቱሪዝም ሀብቷን በውጭው አለም በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ ርቀት አልተጓዘችም ብለዋል።

በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በዲጂታል ዲፕሎማሲው በመታገዝ የቱሪዝም ሀብቶቻቸውን በስፋት በማስተዋወቅ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤" በውጭ ሀገር ተመድበን የምንስራ ዲፕሎማቶች ታላቅ አደራና ሃላፊነት አለብን" ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያን ቱሪዝም ከዲጂታል ዲፕሎማሲው ጋር በማስተሳሰር ለአለም ህዝብ በማስተዋወቅ ረገድ በሰፊው ለመስራት ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

''ጎርጎራ፣ ኮይሻና ወንጪ የመሳሰሉ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በውጭው አለም በማስተዋወቅ ረገድ ዲፖሎማቶች በትኩረት እንሰራለን'' ያሉት ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዲፕሎማትነት የሚሰሩት ሙሉጌታ ተስፋሁን ናቸው፡፡

ዲጂታል ዲፕሎማሲውን በመጠቀም የኢትዮጵን የቱሪዝም መስህቦች ማስተዋወቅ ለኢኮኖሚ እድገቱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው፤ "ዲጂታል ቴክኖሎጂውን በፍጥነት መቀላቀል ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው "ብለዋል፡፡

የዲፕሎማቶቹ ጉብኝት ዓላማ እንደ ሀገር ያሉንን የቱሪዝም ፀጋዎች በዲጂታል ዲፕሎማሲው በመታገዝ በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው ያሉት ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ናቸው።

ተቀዛቅዞ የቆየውን የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ዲፕሎማቶች በሚሄዱባቸው ሀገራት የገጽታ ግንባታ ስራዎችን በማከናወን የውጭ ጎብኚዎችን ፍሰት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

70 አባላትን ያቀፈ በውጭ ሀገራት ተመድበው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች ቡድን በጎንደር ከተማ የሚገኘውን የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት ጨምሮ የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክትን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም