ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በትምህርቱ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

ህዳር 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) ትምህርት ሚኒስቴር ከደቡብ ሱዳን የከፍተኛ ትምህርት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በትምህርቱ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል።

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከደቡብ ሱዳን የከፍተኛ ትምህርት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጋብርኤል ቻንግሰን ቻንግ ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የምትሰጠውን ነጻ የትምህርት እድል ለማሳደግ ያስችላል።

ስምምነቱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የትምህርት ዘርፍ የቆየ ትብብርና ወዳጅነት የበለጠ እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።

የደቡብ ሱዳን የከፍተኛ ትምህርት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጋብርኤል ቻንግሰን ቻንግ በበኩላቸው ሰነዱ ሁለቱ አገራት በትምህርት መስክ ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሳድገው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሚሰጠው ነጻ የትምህርት እድል በርካታ ደቡብ ሱዳናውያን የነጻ ትምህርት ተጠቃሚ እንደሆኑ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም