የደመወዝ ጭማሪ፣ የደረጃ እድገትና ጥቅማ ጥቅም ይከበርልን----የሶማሌ ክልል መምህራን

ጅግጅግ መስከረም 17/2011 መንግስት የፈቀደልን የደመወዝ ጭማሪ፣ የደረጃ እድገትና ጥቅማ ጥቅም ይከበርልን ጥያቄያችን ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ በሶማሌ ክልል የሚገኙ መምህራን ጠየቁ። የክልሉ መንግስት በበኩሉ የመምህራንን መብትና ጥቅም ለማስከበር በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቋል ። በመምህራን መብትና በ2011 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ውይይት ሰሞኑን በጅግጅጋ  ከተማ ተካሂዷል ። በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ መምህራን በክልሉ የመምህራን ደመወዝ ዘግይቶ የሚከፈል ቢሆንም የሐምሌና የነሀሴ 2010 ዓ.ም ደመወዝ እስካሁን ሳይከፈላቸው ቆይቷል። መንግስት የፈቀደላቸውን የደመወዝ ጭማሪ፣ የደረጃ እደገትና ጥቅማ ጥቅም ላለፉት አራት ዓመታት ሳያገኙ በመቆየታቸው በተደጋጋሚ ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም ምላሽ ሳያገኙ መቆየታቸውን ተናግረዋል ። የዶክተር አብዱል መጅድ ሁሴን መምህራን ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ መምህርና የክልሉ መምህራን ማህበር የቀድሞ  ፕሬዚዳንት አቶ ገጄል ቆረነ የክልሉ መምህራን  ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ይሰተካከልለን በሚል በተደጋጋሚ በማህበሩ አማካኝነት ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር አሰታውሰዋል ። “የቀድሞ የክልሉ አመራሮች ለመምሀራኑ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የማህበሩን አመራሮች ለእስር ዳርገው መብታችንን አፍነዋል” ሲሉም አስረድተዋል። “የቀድሞ የክልሉ አመራር የመምህራንን የመብት ጥያቄዎች በቅንነት ከመመልከት ይልቅ እንደ ወንጀል ሲመለከተው ቆይቷል” ያሉት ደግሞ በጅግጅጋ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት መምህር ገብሬ ገብረማርያም ናቸው። በሌሎች ክልሎች የሚገኙ መምህራን ያገኙትን የደመወዝ ጭማሪ፣ የመኖሪያ ቤትና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በክልሉ የሚገኙ መምህራን ሳያገኙ መቆየታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ። መምህራን ከአዲሱ የክልሉ አመራር ጋር ፊትለፊት መወያየታቸው  የቆዩ የመብትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻቸው መፍትሄ ያገኛሉ የሚል እምነት እንዳሳደረባቸው መምህር ገብሬ ገልፀዋል ። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳር አቶ አደን ፋራህ  በበኩላቸው ከመምህራኑ ለተነሱ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች በሰጡት ምላሽ አዲሱ የክልሉ አመራር የነበረውን ብልሹ አሰራር ለማስተካከል እየሰራ ነው፡፡ “የክልሉ መንግስት የትምህርት አስፈጻሚውን በመገምገም ለዘርፉ እድገት ጥሩ አመለካከትና ክህሎት ያላቸውን አካላት የመደበ በመሆኑ የመምህራን ሙያና ጥቅም እንዲከበር አመቺ ሁኔታ ተፈጥራል “ ብለዋል። መምህራን ያለ ፍቃዳቸው ከደመወዛቸው ምንም አይነት መዋጮ እንደማይቆረጥባቸው የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳሩ መምህራን ትውልድን የሚቀርፁ በመሆናቸው ህብረተሰቡ በህገ መንግስቱ የተረጋገጡለትን መብቶች በትክክል እንዲገነዘብ መስራት እንዳለባቸው አሳሰበዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ሰላም በመፈጠሩ መምህራን ያለስጋት ወደ ሥራ ገበታቸው ተመለሰው የዓመቱ ትምህርት እንቅስቃሴ የተሳካ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ጠይቀዋል ። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲቃድር መሀመድ በበኩላው ከዚህ ቀደም በአመራሩ ዘንድ ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት ሳይሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል ። “ቀድሞ በነበረው አመራር ችግር የመምህራን ደመወዝ፣ የደረጃ እድገትና ጥቅማ ጥቅም  ባለመከበሩ  በትምርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሲያሳድር ቆይቷል ” ብለዋል ። የመምህራን ክብር፣ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅና ለጥያቄዎቻቸው ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ቢሮው ከክልሉ መንግስትና መምህራን ማህበር ጋር በመሆን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አመልክተዋል። መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች የተማሪዎችን አንድነት በማጠናከር ትምርት ቤቶች ከስጋት ነፃ እንዲሆኑ የበኩላቸውን እንዲወጡ የቢሮው ኃላፊ ጥሪ አቀርበዋል ። በውይይት መድረኩ ላይ በክልሉ በየደረጃው ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከ200 መቶ በላይ መምህራን መሳተፋቸውን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም