የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀጣይ ዐቢይ ተግባራትን የክንውን ጊዜ ሰሌዳ ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀጣይ ዐቢይ ተግባራትን የክንውን ጊዜ ሰሌዳ ይፋ አደረገ
አዲሰ አበባ ( ኢዜአ) ህዳር 21/2015 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀጣይ ዐቢይ ተግባራትን የክንውን ጊዜ ሰሌዳ ይፋ አደረገ።
በዚህም እስከ ታህሳስ 2015 የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ፣ በጥርና የካቲት ወራት አጀንዳ ማሰባሰብ ፣ ከየካቲት እስከ መጋቢት 2015 የምክክር አጀንዳዎችን ቀረፃ ማጠናቀቅ እንዲሁም በመጋቢት 2015 ዓ.ም ሀገራዊ ምክክሮችን ይከናወናሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ክንውኑን እና የስራ ዕቅዱን አቅርቧል፡፡
ሪፖርቱን ያቀረቡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዳሉት በቀዳሚነት ኮሚሽኑ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር መሰረት የሚሆን ምክክር ለማድረግ የሚረዱ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
በምክክር ሂደቱ የተሳታፊዎች መለያና፣ የአጀንዳ አሰባሰብ ስርዓትን በተመለከተ በክልል፣ በከተማ አስተዳደሮች ፣ በፌዴራልና ዳያስፖራ በሚል በተለዩ አራት የትኩረት አቅጣጫዎች እኩል የአፈፃፀም ስርዓት ይከተላል ነው ያሉት።
ተሳታፊዎችም የፖለቲካ መሪዎች፣ የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ሲሆኑ ጥናቶችን ማካሄድ፣ የተሰሩ ስራዎችን ማሰባሰብ፣ በመልዕክት(ኢሜል፣ፖስታ በአካል)፣ ህዝባዊ ውይይቶች አጀንዳ የማሰባሰብና ማደራጀት ስራዎች ይከናወናሉ ነው ያሉት።
በምክክር ሂደቱ ሁሉም ህብረተሰብ ክፍሎች እኩል ተሳትፎና ተደማጭነት ይኖራቸዋል ተብሏል።
ከህዳር እስከ ጥር ባሉት ወራቶች አወያዮች እና አመቻቾችን የመመልመል ስራ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
እንዲሁም በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም ሀገራዊ ምክክሮችን የማካሄድ ሂደት እንደሚጀመር ተናግረዋል።