የደምቢዶሎ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

133
ግንቦት 12/2010 በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን የደንቢዶሎ አውሮፕላን ማረፊያ ዛሬ መደበኛ የበረራ አገልግሎት መጀመሩን በኢትየጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሙሀመድ በቀለ አስታወቁ፡፡ በ176 ሚሊየን ብር የተገነባው አየር መንገድ ግንባታው በሁለት ፈረቃ ሌት ከቀን በመሰራቱ ከተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ቀድሞ መጠናቀቁንም ነው ስራ አስኪያጁ ያብራሩት፡፡ ግንባታው 98 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን የአጥር፣ ማማና ማረፊያ ግንባታዎች  በብረት እጥረት ምክንያት መጓተታቸውን ገልጸው በቀጣዮቹ ሁለታ ወራት ውስጥ ቀሪ ስራዎች እንደሚጠናቀቁ ተናግረዋል፡፡ 2.18 ኪሎ ሜትር በ30 ሜትር ስፋት ያለው የኼው የአውሮፕላን ማረፊያ በአንድ ጊዜ ሁለት አውሮፕላኖችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን በየሳምንቱ ሶሰት ጊዜ የበረራ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የደምቢዶሎ አየር ማረፊያ ስራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ውለታው በበኩላቸው አውሮፕላን ማረፊያው ሰኔ 18/2008 በኮረኮንች ደረጃ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውሰው የተገልጋዮችን ምቾትና ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ወደ አስፓልት መቀየሩን ተናግረዋል፡፡ አውሮፕላን ማረፊያው ለአካባቢው ህዝብ፣ ለአየር መንገዱና ለሀገሪቱ  ትልቅ ሃብት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሀንዲስ ዳዊት ጠንክር እንዳሉት 10 ሴንቲ ሜትር ውፍረት ያለው የአስፓልት ንጣፍ ለ30 ዓመታት አስተማማኝ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በአካባቢው የሚገኝ ጠጠር በቤተ ሙከራ ተፈትሾ የጥራት ደረጃው አስተማማኝ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ለግንባታው ጥቅም ላይ መዋሉንም አብራርተዋል፡፡ ግንባታው ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ  የሙያ ባለቤት እንዲሆኑም አግዟቸዋል ነው ያሉት ተቆጣጣሪ መሀንዲሱ፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች የፌደራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን የያዘው አውሮፕላንም ከደቂቃዎች በፊት ደምቢዶሎ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሱን በቦታው የምትገኘው ሪፖርተራችን ያደረሰችን ዘገባ ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደንቢዶሎውን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ደረጃቸውን የጠበቁ 21  የበረራ መዳረሻዎች  አሉት፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም