ቀጥታ፡

የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትን መግታት አሁንም ትኩረት ይሻል---የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ(ኢዜአ)ህዳር 21/2015 በኢትዮጵያ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትን መግታት አሁንም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ12 ሺህ በላይ ዜጎች በኤች. አይ .ቪ /ኤድስ እንደሚያዙም ነው ሚኒስቴሩ የጠቆመው፡፡

የዓለም የኤድስ ቀን ''በቂ የማህበራዊ እንዲሁም የባህሪ ለውጥ መረጃዎች የኤች. አይ.ቪ ምርመራና ተደራሽነት በትምህርት ቤትና ከትምህርት ቤት ውጭ ላሉ ልጃገረዶችና ወጣቶች'' በሚል መሪ ሃሳብ   እየተከበረ ነው።

የጤና ሚኒስቴር ድኤታ ጽህፈት ቤት ኃላፊና ከፍተኛ አማካሪ አቶ ፈቃዱ ያደታ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ የበሽታው ስርጭት ከሶስት በመቶ በላይ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ለዚህ ደግሞ ለበሽታው የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን እንደምክንያት ይጠቀሳል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ስርጭቱ ወደ 0 ነጥብ 92 በመቶ ዝቅ ቢልም ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ12 ሺህ በላይ ዜጎች በኤች. አይ.ቪ /ኤድስ እንደሚያዙ አመልክተው ከዚህ ውስጥ 69 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት የበሽታውን ስርጭት መግታት ይገባል ነው ያሉት፡፡

የኤድስ ጤና ፋውንዴሽን በተሰኘው ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት መንግስቱ ገብረሚካኤል፤የበሽታው ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም እንደ አዲስ የሚያዙ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ለዚህም አንዱ ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ግንዛቤ በማሳደግ አንጻር ክፍተቶች መኖራቸው እንደሆነም ገልፀዋል።

በዚህም በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች በሽታው አሁንም ወረርሽኝ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሆነ አንስተው፤ ከዚህ አኳያ የኀብረተሰቡን ባህልና እውቀት መሰረት ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ማከናወን ይገባል ብለዋል።

የዓለም የኤድስ ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ35ተኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ34ተኛ ጊዜ ነው እየተከበረ የሚገኘው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም