ሌብነትን የሚጠየፍ ትውልድ ለማፍራት ኃላፊነታችንን የሚመጥን ሥራ ልንሰራ ይገባል - ተቋማቱ

78

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 21 ቀን 2015 ሌብነትን የሚጠየፍ ትውልድ ለማፍራት ማህበረሰቡን በማስተማርና በግብረ ገብነት በማነጽ ኃላፊነታችንን የሚመጥን ስራ ልንሰራ ይገባል ሲሉ በሲዳማ ክልል የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ገለፁ።

ሌብነትና ሙስና እንደሀገር አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱንና ለዚህም ተገቢው እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ መናገራቸው ይታወሳል።

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲዳማ ክልል የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በእጃቸው ያለውን ምዕመን በማስተማርና በግብረ ገብነት በማነጽ ሀገሪቱ ከገባችበት ችግር የማውጣት ሃላፊነታቸውን የሚወጡበት ወቅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀዋሳ ከተማና ዙሪያ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የሲዳማ ክልል የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ላዕከ ወንጌል ቀሲስ ደግፌ ባንቡራ "ሌብነት ህዝብን ለማገልገል ተቆጥሮ የተሰጠንን ሰዓት ከመስረቅ ይጀምራል" ይላሉ።

"ሌብነት የልምምድ ውጤት ነው" ያሉት ቀሲስ ደግፌ፤ ነገ ገዝፈው ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥሉ የሙስና ወንጀሎች የሚፈፀሙት በትንሽ በትንሹ ስርቆትን ባዳበሩ ግለሰቦች ነው ብለዋል።

በተለይም የሐይማኖት ተቋማት በዚህ ትግል ላይ የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ እንዳለባቸው አመልክተው በየቤተ እምነታቸው ትውልድን የማነፅና ብልሽቶችን የማከም ሥራ መስራት ከራስ ይጀምራል ብለዋል።

የሐይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው ከራስ ጀምረው በመስራት አርአያ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የሲዳማ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰብሳቢና የሲዳማ ክልል የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ሁሴን መሀመድ በበኩላቸው "ሌብነት ብዙሃን ድሆችን የዕለት ጉርስ አሳጥቶ የጥቂቶችን ኪስ የሚያደልብ ተግባር" እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህንን የመታገል ኃላፊነት ደግሞ "የሁሉም ተቋማትና ግለሰቦች ነው" ያሉት ሼህ ሁሴን፤ በተለይም የዕምነት ቤቶች ይህን በማረም ረገድ የሚመጥነን ስራ የምንሰራበት ወቅት ላይ ነን ብለዋል ።

በመሆኑም ምዕመናኑን  በማስተማርና  በመገሰጽ  ሀገራችን  ከገባችበት ችግር   ማውጣትና ዜጎቻችን ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጋር እንዲዛመዱ የሚመጥን ስራ ልንሰራ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

"የመልካም ባህልና ዕሴት ባለቤት ከሆንን ህዝብ ሌብነት አይጠበቅም" ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የማዕከላዊ ደቡብ ኢትዮጵያ ሲኖዶስ ፕሬዝዳንትና የሲዳማ ክልል የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል ቄስ ኢያሱ ጠጊቾ ናቸው።

በአሁን ወቅት እንደ ሀገር "በስፋት እየተስተዋለ ያለው ሌብነትና ብልሹ አሰራር አብዛኛው ህዝቧ በቤተ እምነቶች ቅኝት ውስጥ የሚኖርባት ኢትዮጵን የማይመጥን ተግባር ነው" ሲሉም አንስተዋል።

ቤተክርስቲያኗ ምዕመናኑን በማስተማርና በመግራት የሚጠበቅባትን ለመወጣት ትሰራለችም ብለዋል።

መንግስት እንደሀገር አስከፊ ደረጃ የደረሰውን የሙስናና ሌብነትን ለመከላከል ሀገራዊ ኮሚቴ ማቋቋሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም