ቀጥታ፡

ሀዋሳ ለበዓሉ መሰናዶዋን አጠናቃለች-ከተማ አስተዳደሩ

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 20 ቀን 2015 የፊታችን ህዳር 29 በሀዋሳ የሚከበረውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል በድምቀት ለማክበር የሚያስችለውን መሰናዶ ማጠናቀቁን የከተማዋ አስተዳደር ገለጸ።

የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ የከተማ አስተዳደሩ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፈሰር ጸጋዬ ቱኬ በመግለጫቸው የከተማው አስተዳደርና ሕዝቡ ለበዓሉ በድምቀት መከበር ልዩ ትኩረት ሰጥተው ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት የሚካሄድ መሆኑን በመግለፅ እለቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት የተረጋገጠበት ቀን በመሆኑ በዓሉ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል ነው ያሉት።

በመሆኑም የሁሉም ክልል ሕዝቦች የሠላምና የልማት መሠረት የሆነውን በዓል በድምቀት ለማክበር ሀዋሳ አስፈላጊ መሰናዶዎችን አጠናቃ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅታለች ብለዋል።

ከተማዋ ትልቅ ቦታና ትርጉም የሚሰጠውን በዓል ለማሰናዳት እድል በማግኘቷ ከንቲባው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ምስጋና አቅርበዋል።

በዓሉ በከተማዋ መከበር ትልቅ እድል ይዞ ይመጣል ያሉት ከንቲባው በተለይም ለመላው ኢትዮጵያውያን ሀዋሳ ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድ፣ ለቱሪዝም፣ ለኮንፍረንስና ለኑሮ አመቺ መሆኗን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ታላቅ መድረክ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

ከተለያዩ ክልል የተውጣጡ የብሄር ብሄረሰብ ተወካዮች እና የስራ አመራሮች በተገኙበት የሚከበረውን ታላቅ በዓል በሰላም ለማክበር በፀጥታው ረገድም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በንግዱ ማህበረሰብም የዋጋ ቅናሽ ከማድረግ ጀምሮ ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች የቆይታ ጊዜያቸው ያማረ እንዲሆን በተሻለ መስተንግዶ ለመቀበል ተሰናድተናል ብለዋል።

ከንቲባው አክለውም የከተማዋ ወጣት አደረጃጀቶችና የሰላም አምባሳደሮች እንዲሁም ነዋሪዎች ሀዋሳ የፍቅር፣ የአንድነትና የአብሮነት ከተማ መሆኗን በሚያሳይ መልኩ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት።

ህብረተሰቡ በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶቿንና የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን በአክብሮት፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በቆየ አብሮ የመኖር እሴትን በሚያንፀባርቅ መልኩ እንዲቀበሉም ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።

በየዓመቱ የሚከበረው ህዳር 29 በዓል በብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር ብሎም ትስስራቸውን ለማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ17ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ ከንቲባው መልእክት አስተላልፈዋል።

በአከባበር ሂደቱም በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች በቀጥታ በበዓሉ ላይ በመሳተፍ ባህላዊ ጭፈራዎችን አልባሳቶችንና የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን ለእይታ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

አገር አቀፍ ሲምፖዚየሞች፣ ዐውደ ርዕዮች፣ ባህላዊ ትርኢቶች እና የባህል ልውውጦች በክብረ በዓሉ ላይ እንደሚካተቱም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም