የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ “ተጨባጭ እና ተግባራዊ” ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን እንዲያዘጋጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ “ተጨባጭ እና ተግባራዊ” ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን እንዲያዘጋጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጠየቁ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 20 ቀን 2015 17ኛው የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ “ተጨባጭ እና ተግባራዊ” ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን እንዲያዘጋጅ የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጠየቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ እያስተናገደች ባለችው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ከ17ኛው ኢንተርኔት አስተዳደር ጉባዔ አምስቱ ንዑስ መሪ ሃሳቦች ጋር በተጣጣመ ቁልፍ የዕድገት ጉዞዎች የታጀበ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ሽፋን በፈረንጆቹ 2017 ከነበረው 19 ሚሊየን ተጠቃሚዎች በ2022 ወደ 30 ሚሊየን ከፍ ማለቱንም ተናግረዋል፡፡
የ4ኛው ትውልድ ወይም 4ጂ ኔትወርክ ህዝብ በሚበዛባቸው ከተሞች እና 5ኛው ትውልድ ወይም 5ጂ ኔትወርክን በትላልቅ ከተሞች መዘርጋቱ ግንኙነቱን እያፋጠነ ነው ብለዋል።
በመላ ሀገሪቱ 2 ሺህ300 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የኢንተርኔት አገልግሎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።