የቻይና መንግስት ከ600 ሺህ ዶላር በላይ የሚገመት ወንጀልን መከላከል የሚያስችል ድጋፍ ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አደረገ

54

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 20 ቀን 2015 የቻይና መንግስት ከ600 ሺህ ዶላር በላይ የሚገመት ወንጀልን መከላከል የሚያስችል ድጋፍ ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አደረገ።

ከቻይና መንግስት የተደረገው ድጋፍ ከስድስት መቶ ሺ የአሜሪካን ዶላር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው  ተሽከርካሪዎችን ትጥቆች መሆናቸውም ተጠቅሷል።

ድጋፉ አምስት ኮሮላ ክሮስ ፓትሮል ተሽከርካሪዎች፣ ጥይት መከላከል የሚችል አንድ ተሽከርካሪ፣ የግንኙነት ማሻሻያ ስርዓት፣ ዲጂታል የፎረንሲክ ላብራቶሪ መሣሪያዎችን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።

ድጋፉን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ዣኦ ዥዩዋን ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አስረክበዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በርክክቡ ሥነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ቻይና የቆየ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሀገራዊ የኢንቨስትመንት ደህንነት ተጠብቆ የበለጠ እንዲሳለጥ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ፌዴራል ፖሊስ ኃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ በቴክኖሎጂ መደገፋ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም ጨምረው አስታውቀዋል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም ሽብርተኝነት፣ የባህር ላይ ውንብድና እና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ የደህንነት ስጋት ከመሆን ባለፈ በኢንቨስትመንትና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ኪሳራ በማድረስ ለሕዝብና ለሀገር ቀውስ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

ወንጀልን ለመከላከልና ለመመርመር የሚያስችሉ፣ የትራንስፖርት ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችሉ የደህንነት መሣሪያዎች፣ የፎረንሲክ ክፍልን የሚያጠናክሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እና በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ረገድ በቻይና መንግስት ለተደረጉ ድጋፎች ኮሚሽነር ጀነራሉ ምስጋና አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዥዩዋን በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት መልካም ግንኙነት ለብዙ ዘመናት የዘለቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የኢትዮጰያ ፌዴራል ፖሊስ የጀመረውን የለውጥ ጉዞ የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል የቻይና መንግስት በቀጣይ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ድጋፎች እንደሚያደረግም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር የተመራው የልዑካን ቡድን አባላትም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እያደረገ ያለውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም