አምስቱ ወንድማማች የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ክስተቶች

307

በኳታር አዘጋጅነትን እየተካሔደ የሚገኘው 22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ዛሬ 10ኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን ያልተጠበቁና ያልተገመቱ ውጤቶች፣ የዳኞች የባከነ ሰአት ጭማሬ እንዲሁም የደጋፊዎች ዝማሬና ሕብረ ቀለም ለዓለም ዋንጫው ድምቀት ከሰጡት ጉዳዮች መካከል ሲሆን ከዕለት ወደ ዕለትም የስፖርቱን አፍቃሪዎች ቀልብ በመሳብ ላይ ይገኛል።

የዘንድሮው ዓለም ዋንጫ እውነታ ብቻ ባይሆንም በአንድ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የሚጫወቱ ወንድማማቾች ጉዳይ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ቀልብ ስቧል። በተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ እየተሳተፉ ያሉት አምስት ጥንድ ወንድማማቾችም የዚህ ክስተት ማሳያ ናቸው።

ጥቋቁሮቹ ከዋክብቶች በሚል ቅጽል ስያሜ የሚጠራው የጋና ብሔራዊ ቡድን አንድሬ አየውና ጆርዳን አየው ከወንድማቾቹ ተጫዋቾች መካክል ይገኙበታል።

የ32 ዓመቱ የክንፍ መስመር ተጫዋች አንድሬ አየው በኳታር ሊግ ለአል ሳድ የሚጫወት ሲሆን በአንድ ዓመት የሚያንሰው ታናሹ ጆርዳን አየው ለእንግሊዙ ክሪስታል ፓላስ በአጥቂ መስመር ይጫወታል።

አንድሬ አየው በምድብ ስምንት ጋና በፖርቹጋል 3 ለ 2 ስትሸነፍ ግብ ማስቆጠሩ ይታወቃል።

አንድሬ አየው ለሶስተኛ ጆርዳን አየው ለሁለተኛ ጊዜ በዓለም ዋንጫው በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ሁለቱ ወንድማማቾች የጋና የቀድሞ ኮከብ ተጫዋች አብዲ ፔሌ ልጆች ናቸው።

የወቅቱ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ፈረንሳይ ስብስብ ውስጥ ሉካስ ሀርናንዴዝና ቲዮ ሀርናንዴዝን እናገኛለን።

ሁለቱ ወንድማቾች በግራ መስመር ተመላላሽነት ይጫወታሉ።

የ26 ዓመቱ ሉካ ሀርናንዴዝ ለጀርመኑ ባየር ሙኒክ በእድሜ በአንድ ዓመት የሚያንሰው ቲዮ ሀርናንዴዝ ለጣልያኑ ኤሲ ሚላን ክለብ ይጫወታሉ።

ሉካ ሀርናንዴዝ ፈረንሳይ አውስትራሊያን 4 ለ 1 ባሸነፈችበት የመጀመሪያ ጨዋታ ባጋጠመው የሊጋመንት (ጅማት) ጉዳት ከሜዳ የወጣ ሲሆን ወንድሙ ቲዮ ተክቶት ወደ ሜዳ ገብቷል’

ሉካ ባጋጠመው ጉዳት ከዓለም ዋንጫው ውጪ የሆነ ሲሆን የደረሰበት ጉዳት ክብደት ራሱን ከእግር ኳስ ለማግለል እንዲያስብ አድርጎታል ሲል የፈረንሳዩ ዕለታዊ የስፖርት ጋዜጣ ለኪፕ በዘገባው አሰፍሯል።

ንስሮቹ በሚል ቅጽል ስያሜ የሚጠራው የሰርቢያ ብሔራዊ ቡድን የሚገኙት ሰርጋይ ሚሊንኮቪች ሳቪች እና ቫንያ ሚሊኒንኮቪች ሳቪች በዓለም ዋንጫው እየተጫወቱ የሚገኙ ወንድማማቾች ናቸው።

የ27 ሰርጋይ ለጣልያኑ ላዚዮ ክለብ አማካይ ስፍራ የሚጫወት ሲሆን በሁለት ዓመት የሚያንሰው ታናሹ ቫንያ በጣልያኑ ቶሪኖ ክለብ በግ ጠባቂነት ይጫወታል።

ሁለቱ ወንድማቾች ሰርቢያ በምድብ ሰባት ከብራዚልና ካሜሮን ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች ተሰልፈዋል።

ሰርጋይ ሚሊንኮቪች ሳቪች ትናንት ሰርቢያ ከካሜሮን 3 ለ 3 በተለያይችበት ጨዋታ ግብ ማስቆጠሩ ይታወቃል።

ቫንያ ሚሊንኮቪች ሳቪች ንስሮቹ በብራዚል 2 ለ 0 በተሸነፉበት ጨዋታ ያለቀላቸውን የግብ እድሎች በማዳን ሰርቢያ ብዙ ግሎች እንዳይቆጠሩበት አድርጓል።

በፊፋ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘውና ወርቃማው ትውልድ እየተባለ በሚጠራው የቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን ኤደን ሃዛርድና ቶርጋን ሀዛርድን እናገኛቸዋለን።

ሁለቱን ወንድማማቾች የሚያመሳስላቸው በተመሳሳይ የአጥቂ አማካይ ስፍራ መጫወታቸው ነው።

የ31 ዓመቱ ኤደን ሀዛርድ በስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ እንዲሁም የ29 ዓመቱ ቶርጋን ሀዛርድ ለጀርመኑ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ይጫወታሉ።

ወንድማቾቹ በዓለም ዋንጫው ሲሳተፉ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፏቸው ሩሲያ እ.አ.አ በ2018 ባዘጋጀችው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ነበር።

ኤደን ሀዛርድ ከዘንድሮው ዓለም ወንጫ በኋላ ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ እንደሚያገል መግለጹ ይታወቃል።

አምስተኛና የመጨረሻውን የሚለያቸው ወንድማቾቹ የሚጫወቱት ለአንድ አገር አይደለም። ነገር ግን የሚጫወቱት ለአንድ ክለብ። እሱም ለስፔኑ አትሌቲኮ ቢልባኦ ነው።

ኢናኪ ዊሊያምስ እና ኒኮላስ ዊሊያምስ በቅደም ተከተል በ22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ጋና እና ስፔን ወክለው ተሳትፈዋል።

ታላቁና የ26 ዓመቱ ኢናኪ ዊሊያምስ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ሲሆን እ.አ.አ በ2016 ለስፔን ከ21 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫውቷል።

ኢናኪ ለስፔን ወጣት ብሔራዊ ቡድን ብቻ ሳይሆን እ.አ.አ በ2016 በወቅቱ የስፔን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በነበሩት ቪሴንቴ ዴልቦስኬ ጥሪ ተደርጎለት ስፔን ቦሲኒያ ሄርዞጎቪን 3 ለ 1 ባሸነፈችበት የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ተጫውታል።

የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ከቦሲኒያው ጨዋታ በኋላ በስፔን ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎለት አያውቅም።

ኢናኪ ዊሊያምስ በአንድ ወቅት “ቤተሰቦቼ ከጋና ናቸው ነገር ግን የማውቀው ተወልጄ ያደጉበትን የስፔን ባህል ነው መቶ በመቶ የጋናዊነት ስሜት አይሰማኝም” የሚል አስተያየት ሰጥቶ ነበር።

ይሁንና አጥቂው ሀሳቡን በመቀየር እ.አ.አ በ2022 መግቢያ ለአፍሪካዊቷ አገር ጋና ለመጫወት ዝግጁ መሆኑን የገለጸ ሲሆን የጥቋቁሮቹ ከዋክብቶች አሰልጣኝ ኦቶ ኦዶ ጥሪ ተደረገለት።

ጋና በመስከረም ወር 2015 ዓ.ም በብራዚል 3 ለ 0 በተሸነፈችበት ጨዋታ ተሰልፎ የመጀመሪያ ጨዋታውን አደረገ።

ወደ ኳታር ወዳቀናው የጋና ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ተካቶ በምድብ ስምንት ጥቋቁሮቹ ከዋክብቶች ከፖርቹጋልና ኮሪያ ሊፐብሊክ ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል።

የ20 ዓመት ታናሽ ወንድሙ ኒኮላስ ዊሊያምስ ፓምፕሎና በምትባል የስፔን ከተማ የተወለደ ሲሆን እንደ ታላቅ ወንድሙ በስፔኑ አትሌቲኮ ቢልባኦ የእግር ኳስ አካዳሚ ነው ያለፈው።

የክንፍ መስመር ተጫዋቹ ኒኮ በስፔን ከ18፣19 እና 21 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች ተጫውቷል።

ኒኮላስ ዊሊያምስ በስፔን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሉዊስ ኤነሪኬ በ2022/23 የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ውድድር ጥሪ ተደረገለት።

ከዓለም ዋንጫው በፊት ስፔን ጆርዳንን 3 ለ 1 ባሸነፈችበት ጨዋታ የመጀመሪያ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል።

ኒኮላስ ዊሊያምስ ስፔን በዓለም ዋንጫው ከኮስታሪካ እና ጀርመን ጋር ባደረገችው ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ተጫውቷል።

የኮትዲቭዋሮቹ ያያ ቱሬና ኮሎ ቱሬ፣ክሮሻውያኑ ኒኮ ኮቫች እና ሮበርት ኮቫች፣ የኔዘርላንዶቹ ሮናልድ ኪዩማንና ኤርዊን ኪዩማን እንዲሁም የግብጾቹ ሆሳም ሀሰንና ኢብራሂም ሀሰን በዓለም ዋንጫ ከተጫዋቱ ወንድማማቾች መካከል ይገኙበታል።

እ.አ.አ በ1954 በስዊዘርላንድ አስተናጋጅነት በተካሄደው አምስተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለጀርመን(በወቅቱ ምዕራብ ጀርመን) ብሔራዊ ቡድን የተሰለፉት ኦትማር ዋልተርና ፍሪትዝ ዋልተር በዓለም ዋንጫ የተጫወቱ የመጀመሪያዎቹ ወንድማማቾች

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም