ቀጥታ፡

የአርብቶ አደር የምግብና ስርዓተ ምግብ ደህንነት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 20 ቀን 2015 በአርብቶ አደር አካባቢ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል የአርብቶ አደር የምግብና ስርዓተ ምግብ ደህንነት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

የፕሮግራሙ ማስጀመሪያ  በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን፣ የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሃመድ፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ልማትና የቢዝነስ አቅርቦት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱል ካማራ ፣ ከፌደራልና ከክልል የተወጣጡ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

May be an image of 9 people, people sitting and people standing

በዚሁ ወቅት እንደተገለጸውም ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ቀንድ የምግብ ደህንነት ችግርን የመቋቋም አቅምን በመገንባት የሴቶች፣ የወጣቶችና የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ይችላል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ከማሳደግ ባለፈ በአርብቶ አደር አካባቢ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑም ተጠቁሟል።

ፕሮጀክቱ አጠቃላይ የአርብቶ አደሩን ህይወት በማሻሻል በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ ያስችላልም ተብሏል።

በምስራቅ አፍሪካ የአርብቶ አደሩን ምርታማነት ከማሳደግ አንጻርም ላቀ ያለ ሚና እንደሚኖረውም ተጠቁሟል።

ፕሮጀክቱ ለስድስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን በሶማሌ፣ አፋር ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የሚተገበር መሆኑም ተመልክቷል።

በፕሮጀክቱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመው፤ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 46 ሚሊዮን ዶላር ከአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡  

የአፍሪካ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ መንግስት ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውም በስነ -ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም