ዞኑ የወባ በሽታን ለመከላከል የጸረ-ወባ ኬሚካል ርጭት እያደረገና የአልጋ አጎበር እያከፋፈለ መሆኑን ገለጸ

258

ነገሌ (ኢዜአ) ህዳር 20 ቀን 2015 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የወባ በሽታን ለመከላከል የጸረ-ወባ ኬሚካል ርጭት እያደረገና የአልጋ አጎበር እያከፋፈለ መሆኑን የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በጽህፈት ቤቱ የወባ በሽታ መከላከል ባለሙያ አቶ አለሙ አለታ በዞኑ 6 ወረዳዎች ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወባ መከላከል ስራ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ነው ብለዋል፡፡

ለዚሁ ስራ ከ100 በላይ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ተመድበው የተለያዩ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁንም በ42 ቀበሌዎች ለህዝቡ በአጎበር አጠቃቀም፣ በግልና በአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን አብራርተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ አማካኝነት ከ170 ሺህ በላይ በኬሚካል የተነከረ የወባ መከላከያ አጎበር ለዞኑ ነዋሪዎች መከፋፈሉንም ተናግረዋል።

በተለያዩ ቀበሌዎች ውሀ የተኛበትና ረግረጋማ በሆኑ ስፍራዎች እስካሁን 200 ሄክታር መሬት የሚሸፍን የጸረ-ወባ ኬሚካል ርጭት መካሄዱንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስና ለወባ በሽታ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ረግረጋማ ቦታዎችን የማጽዳት ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።

የሻኪሶ ከተማ ነዋሪው አቶ በላቸው መንዲሳ ከጤና ባለሙያዎች ባገኙት ትምህርት አካባቢያቸውን በማጽዳት በሽታውን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ በቀለ ዱሉ ስለ ወባ በሽታ መከላከያ ዘዴዎች ከጤና ባለሙያዎች ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረው አጎበር መቅረቡንና የቤት ለቤትም የኬሚካል ርጭት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም