የፋይናንስ አገልግሎቶች ደህንነትን ለመጠበቅ ቴክኖሎጂ አበልጻጊ ተቋማት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል-የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር

171

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ደህንነት ለመጠበቅ ቴክኖሎጂ አበልጻጊ ተቋማት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አሳስቧል።

በኢትዮጵያ የሳንቲምፔይ ፋይናንሺያል የክፍያ ስርዓት አገልግሎት ዛሬ በይፋ ስራ ጀምሯል።

የክፍያ ስርዓቱ በኢትዮጵያውያን ወጣት ሳይንቲስቶች የተሰራ ሲሆን የዲጂታል ግብይት የሚከናወንበት እንደሆነ ተገልጿል።

በማስጀመሪያ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትእግስት ሀሚድ እንዳሉት ዛሬ ተግባራዊ የተደረገው የክፍያ አገልግሎት በኢትዮጵያ ያለውን የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በዲጂታል በመተካት ሂደት ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው።

በወጣት ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች ተግባራዊ የተደረገው የክፍያ ስርዓት ሀገሪቱ የጀመረችውን ዲጂታል ኢኮኖሚን የመገንባት ውጥን በማሳካት ረገድ የራሱ ድርሻ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

የሳንቲም ፔይና መሰል የቴክኖሎጂ አበልጻጊ ተቋማት ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከወዲሁ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የክፍያ ስርዓቱ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ተጠቃሚ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል።

በእለቱም ፓስ፣ ዩኒፋይድ ፔይመንት ኢንተርፌስና ፔይመንት ጌት ዌይ የተሰኙ የደጂታል አገልግሎቶች ከስድስት አጋር ባንኮችና ከቴሌ ብር ጋር በመተባበር ወደ ስራ ገብተዋል።

ሳንቲም ፔይ ከተለያዩ ባንኮች በአንድ ጊዜ የተለያዩ ክፍያዎችን መፈጸም የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል።

የሳንቲም ፔይ ድርጅት ከውጭ የሚገቡ የፖስ ማሽንና ለሌሎችም መተግበሪያዎች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ እንደሚቀንስ ተጠቁሟል።

ድርጅቱ በተያዘው ዓመት መጨረሻ የተጠቃሚዎቹን ቁጥር 250 ሺህ ለማድረስ እየሰራ እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም