ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም መስፈን ያላትን ቁርጠኝነት በሚገባ ማስተዋወቅ አለባቸው -አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

99

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም መስፈን ያላትን ቁርጠኝነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚገባ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናገሩ።

በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ዲፕሎማቶች የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ጎብኝተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ  ላለፉት ሶስት ሳምንታት ለመካከለኛና ነባር ዲፕሎማቶች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት ትናንት መጠናቀቁ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም ዲፕሎማቶቹ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እና የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች የመስክ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ዲፕሎማቶቹ በዛሬው ዕለትም የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖን ጨምሮ ሌሎች የተቋሙ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚሁ ጊዜ የኢፌዴሪ አየር ኃይል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ አኩሪ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎችን ስለማከናወኑ አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ያላትን አቅምና ፀጋ በሚገባ ተገንዝበው ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በጉብኝቱ የተሳተፉት ዲፕሎማቶች በበኩላቸው በጉብኝታቸው አየር ኃይሉ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ አኩሪ ስራ እያከናወነ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

በጉብኝታቸው አየር ኃይሉ የሪፎርም ስራዎችን በማከናወን ወቅቱን በሚመጥን መልኩ ዝግጁ ለመሆን እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን መመልከት ችለናል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት በማስጠበቅ አኩሪ ገድል የፈጸመ ተቋምን በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን ደስታም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም