የአምራች ኢንዱስትሪው ማነቆ የሆኑ የመስሪያና መሸጫ ቦታዎችን የማልማት ስራ ይከናወናል- የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት

164

ሐዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ማነቆ የሆኑ የመስሪያና መሸጫ ቦታዎችን የማልማትና የፋይናንስ አቅርቦት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ፡፡

አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለሚደግፉ የሶስት ክልል አመራሮችና ባለሙያዎች የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ዛሬ በሐዋሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የካፒታል እቃ ሊዝና ፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ የሺድንበር ላቀው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አምራች ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ዘርፍ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካትና ወደ ውጭ በመላክ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የስራ እድል በመፍጠር ረገድ የሚኖራቸውን ሚና የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ለማሳደግ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው ደንብ በዘርፉ የሚታዩ ማነቆችን መፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን እንዲያከናውን ስልጣንና ሃላፊነት እንደሰጠው ገልጸዋል።

አሰራሩ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ማነቆ የሆኑ የመስሪያና መሸጫ ቦታዎችን የማልማትና የፋይናንስ አቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ የሚከናወኑ ተግባራትን ያስቀመጠ እንደሆነም ተናግረዋል።

ከክልሎች ጋር በመቀናጀት መሰረተ ልማት የተሟላላቸውን የማምረቻ ቦታዎች መገንባትን ጨምሮ ለክልሎች ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የአምራች ኢንደስትሪዎችን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር ብድር እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ምቹ የፋይናንስ ስርዓት እንዲዘረጋ ይሰራል ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ታደለ ወልደሚካኤል ለኢንተርፕራይዞች ተገቢውን የድጋፍ ማእቀፍ በማዘጋጀት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን እንዲተኩና ጥራት ያለው ምርት አምርተው ወደ ውጭ እንዲልኩ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኢንተርፕራዞቹ ከውጭ የሚገቡ የቤትና የቢሮ እቃዎችን ጨምሮ ባለኮከብ ሆቴሎች የሚጠቀሟቸው የውስጥ እቃዎችን በጥራት ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ በሞሪንጋ ምርትና በእደ ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ሁለት ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ እንደሚልኩ ለአብነት ገልጸዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና በክልሉ 24 የሚደርሱ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች ምርታቸውን ወደ ውጭ የሚልኩ ሲሆን በጨርቃ ጨርቅና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ናቸው ብለዋል፡፡

ዘንድሮም ተጨማሪ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ የሚልኩ አምስት ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢንተርፕራይዞቹን ለመደገፍ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ክልላዊ የኢንዱስትሪ ልማት ምክር ቤት በማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እየተዘጋጀ ያለው የአምራች ኢንዱስትሪ ፍኖተ ካርታና ስትራቴጂክ ፕላን በእውቀት የታገዘ ድጋፍ ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በአምራች ዘርፉ ከ18 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ እታገኝ ወልዴ በዞኑ የማምረቻና መሸጫ ቦታዎችን ጨምሮ በፋይናንስ ዘርፍ የሚታዩ ማነቆዎችን በተገቢው መፍታት ከተቻለ ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለተከታታይ ስድስት ቀናት የሚቆየው ስልጠና የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውን ደንብ ጨምሮ በአምራች ኢንዱስትሪው የክላስተር ማዕከላትና በማምረት አቅም አጠቃቀም ላይ ያተኮሩ ሰነዶች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

ከደቡብ፣ ሲዳማና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የተውጣጡ ከ500 በላይ አመራሮችና ባለሙያዎች በስልጠናው እየተሳተፉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም