በዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ማስተዋወቅ ላይ በስፋት ይሰራል

104

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 ኢትዮጵያ እያስተናገደች በሚገኘው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ መልካም ገጽታን ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ገለጹ።

በቀጣይም ሌሎች ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በጉባኤው ኢትዮጵያ በዲጂታል ልማት እያከናወነች ያለችውን ስራ ከማቅረብ ጎን ለጎን ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደምትቀስም ተናግረዋል።

17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር  በለጠ ሞላ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በጉባኤው ለመታደም ከተለያዩ የዓለም አገሮችና ተቋማት የመጡ ተሳታፊዎች እየተሳተፉ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ ጉልህ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ለአስራ ሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደውን የዓለም የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤን ለማስተናገድ በርካታ ፈተናዎችን ማለፏን አውስተዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ የነበረችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በማድረግ ጉባኤው በሀገራችን እንዳይካሄድ ጫናዎች እንደነበሩ ነው ያነሱት።

ሆኖም በሀገሪቱ የነበረውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ስምምነት ላይ መደረሱና መንግስትም አስቀድሞ ከፍተኛ ጥረት በማድረጉ ጉባኤው በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በስኬት መጀመሩን ገልጸዋል።

በጉባኤው ኢትዮጵያ በዲጅታል ዘርፍ እያከናወነች ያለውንና ሌሎች ተግባራትን የማስተዋወቅ ስራ በሰፊው እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ጉባኤው ከተለያዩ አገሮች የመጡ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የግል ድርጅቶች፣ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሳተፉበት በመሆኑ ኢትዮጵያ ያላትን ልምድ በማካፈል ከሌሎች ትምህርት የምትወስድበት እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ዲጂታል ምጣኔ ሃብትን በመገንባት ፈጣን ልማት ለማምጣት የረጅም ጊዜ እቅድ ነድፋ እየሰራች እንደምትገኝ ሚኒስትሩ አውስተዋል።

በጉባኤው የሚቀርቡ ጥናቶች በዓለም ላይ ኢንተርኔትን በሚመለከት ለሚወጡ ፖሊሲዎች መነሻ ሃሳብ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም