የሰላም ምክር ቤቱ አለመግባባቶችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲጎለብት በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል- የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም

28

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 19/2015 አዲስ የተቋቋመው የሰላም ምክር ቤት በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲጎለብት በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበት የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ተናገሩ።

አገር አቀፉ የሠላም ምክር ቤት ዛሬ በይፋ ተመስርቷል።  

ምክር ቤቱ የሃይማኖት  ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ የጸጥታ  ተቋማት፣ የከፍተኛ  ትምህርት ተቋማት፣ ምሁራን እንዲሁም የፖለቲካ  ፓርቲዎች በአባልነት ያቀፈ ነው።  

በምስረታ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ የተለያዩ  የጸጥታና የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል። 

ምክር ቤቱ በዓይነቱ የመጀመሪያ ሲሆን  በአገሪቷ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ እንደሆነም ተገልጿል። 

የሰላም  ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም  በዚሁ  ጊዜ እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ሰላም  ላይ የሚሰሩ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን ዕድል የሚፈጥር  ነው። 

"ሰላም  የጋራ አጀንዳ፣ መንገድና መዳረሻ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ በመሆኑም ለዘላቂ ሰላም መስፈን ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል። 

በኢትዮጵያ አለመግባባቶች በውይይትና በሰከነ መንገድ የመፍታት ባህል እንዲጎለብትም ምክር ቤቱ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡ 

የሃይማኖት  ተቋማት  ለአገር ሰላም  የሚተጉ ዜጎችን በመገንባት ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አኳያ የሃይማኖት ተቋማት የምክር ቤቱን ስራ እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

የሰላም  ምክር ቤቱ  አገራዊ  ምክክር ኮሚሽን በመደገፍ ረገድ የድርሻውን ሚና መወጣት እንዳለበትም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ቤተክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው የምክር ቤቱ መመስረት በሠላም ግንባታ ሂደቱ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡

የሰላም ግንባታ ሂደት ከተናጥል ጥረት ይልቅ በህብረት እንዲከናወን እንደሚያግዝም ነው ያነሱት፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ ምክር ቤቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሠላም ግንባታ ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ምቹ እድል እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡     

     

ምክር ቤቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ያካተተ መሆኑ ወጣቶችን በሠላም ዙሪያ ለማሳተፍ ዕድል የፈጠረ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጋምቤላ ክልል የሠላም ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ኡጁሉ ኮክ ናቸው።

በኢትዮጵያ  የመጀመሪያው  የሆነውን  የሰላም  ምክር  ቤት ለመመስረት  ባለፉት ሦስት ዓመታት ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።  

ምክር ቤቱ ብሔራዊ መግባባት  እንዲፈጠር መሥራት እንዲሁም የግጭት አዝማሚያ ትንተና እና መፍትሔ  ማመንጨት ላይ  እንደሚሰራም ነው የተገለጸው፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም