በሀገር አቀፉ የራፒድ ቼስ ውድድር ዮሴፍ ክፍሌና አሌካ ፉጃጋ ሻምፒዮን ሆኑ

95

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 በ2015 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የራፒድ ቼስ ውድድር በወንዶች ዮሴፍ ክፍሌ፤ በሴቶች ደግሞ አሌካ ፉጃጋ ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡

3ኛው የቼስ ስፖርት የራፒድና ብሊትዝ የግል የበላይነት ሻምፒዮና ከህዳር 16 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።

በሀገር አቀፉ የራፒድና ብሊትዝ ሻምፒዮና ውድድር ላይ በሁለቱም ምድብ  አሸናፊ የሆኑት ስፖርተኞች ተለይተው ታውቀዋል።

በራፒድ የውድድር ምድብ በወንዶች ዮሴፍ ክፍሌ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ሻምፒን መሆን ችሏል።

እንዲሁም ሰርግዮ ፔረራ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ፤ የ12 ዓመት ታዳጊው ካሌብ ያሬድ ሶስተኛ መውጣት ችሏል።

በሴቶች የራፒድ ውድድር ደግሞ አሌካ ፉጃጋ የ2015 ዓ.ም ሻምፒዮና መሆን ችላለች።

በዚህ ውድድር ልደት አባተ ሁለተኛ እንዲሁም ሩት ለይኩን ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም የብሊትዝ ቼስ ውድድር ደግሞ በወንዶች አዲስ አለም ተመስገን አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ በአንደኝነት አጠናቋል።

ሰርግዮ ፔረራና ለይኩን መስፍን በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ በመውጣት ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በሴቶች  የብሊትዝ ውድድር ልደት አባተ ሻምፒዮና መሆን የቻለች ሲሆን ሰላማዊት ስለሺ ሁለተኛ እንዲሁም ሩት ለይኩን ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቼስ ስፖርት ፌዴሬሽን በውድድሩ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ለወጡ ስፖርተኞች የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት አበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ቼስ ስፖርት ፌዴሬሽን  ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሰይፉ በላይነህ ውድድሩ አንጋፋና ታዳጊ ስፖርተኞች የተሳተፉበት እንደነበር ገልጸዋል።

የቼዝ ስፖርት ከስፖርታዊ ውድድርነት ባሻገር የማሰብ አቅምን ለማጎልበት ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ በተለይ ወላጆች ህጻናት የቼዝ ስፖርትን እንዲለማመዱና እንዲወዳደሩ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በውድድሩ ውጤታማ የሆኑት አብዛኞቹ ስፖርተኞች በትምህርታቸውም ስኬታማ መሆናቸውን በዚህ ረገድ በአስረጂነት አንስተዋል፡፡

በአጠቃላይ በውድድሩ 94 ተወዳዳሪዎች የተካፈሉ ሲሆን፤ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት አዳዲስ ስፖርተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም