ለዓለም ዋንጫ ባታልፍም በውድድሩ ሁሉም ጨዋታዎች ላይ የምትሳተፈው ኢንዶኔዢያ

ኢንዶኔዢያ በ22ኛው የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ካልተሳተፉ ሀገራት መካከል ብትሆንም በውድድሩ ሁሉም ጨዋታዎች በሚባል ደረጃ እየተሳተፈች ነው።

በዓለም ዋንጫ ውድድሩ ሳይሳተፉ ኢንዶኔዢያን በውድድር በመወከል ታሪክ የሰሩት ዜጎቿም “በጣም ኩራት ተሰምቶናል” ሲሉ ለሀገራቸው ክብር የበኩላቸውን በማድረጋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ለኢንዶኔዢያ ኩራት የሆነውን ጉዳይ በተመለከተ ዘገባ የሰራው አልጀዚራ የኢንዶኔዢያ ልጆች ሀገራቸውን ለዓለም ዋንጫ ማሳለፍ ባይችሉም በኳስ ምርታቸው ግን በውድደሩ ተፋላሚ ሆነዋል ብሏል።

ሀገሪቷ የውድድሩ ተሳታፊነትን ያገኘችው በምሥራቅ ኢንዶኔዢያ ማዲየም በተባለች ግዛት በሚገኘው ፒቲ ግሎባል ዌይ በተሰኘ ኩባንያ አማካኝነት ነው።

ኩባንያው በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ላይ “አል ሪህላ” በሚል ስያሜ የሚቀርበውን ኳስ እንደሚያመርት እ.አ.አ በ2020 መገለጹ ይታወቃል።

በዛው ዓመት ኩባንያው ቅርንጫፉን በግዛቲቱ በመክፈትም በዓለም ዋንጫው ያልተሳተፉ ኢንዶኔዢያውያን በኳታሩ የዓለም ዋንጫ አሻራቸውን እንዲያኖሩ እድል ፈጠረላቸው።

የማዲየም ግዛት አስተዳዳሪ አህመድ ዳዋሚ በሰጡት አስተያየት” አል ሪህላ የኩራት ምንጭ ሆኖናል በተጨማሪም ወደ ኳሱ ምርት ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ ለሀገር ውስጥ የገቢ ምንጫችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል” ብለዋል።

የኢንዶኔዢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የማዲየም ግዛት ነዋሪዎች “በኳታሩ ዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ሀገሪቱን በኳስ ምርት በማሳተፍና ገቢን በማመንጨት የዓለም ኢኮኖሚ አንድ አካል ሆነዋል” ሲል ኢንዶኔዢያ ከተሳትፎ ባሻገር ከዓለም ዋንጫው ያገኘችውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅምና ለውድድር ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ገልጿል።

ጉዞ የሚል ትረጉምን የያዘው የዓለም ዋንጫው ኳስ “አል ሪህላ” ከአዲዳስ ኩባንያ ጋር በጥምረት የሚመረት ሲሆን በፊፋ የደረጃ ምደባም 14ተኛው ይፋዊ የዓለም ዋንጫ ኳስ መሆኑም ተመልክቷል።

አል ሪህላ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአካባቢ ብክለትን መከላከል አንዲችል ሆኖ ውሃማ መሠረት ካለው ሙጫና ቀለም የተሰራ መሆኑ በዘገባው ተካቷል።

በቅርብ ዓመታት በተካሄዱ የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ጥቅም ላይ ከዋሉት ኳሶች መካከል የ2006ቱ ቴሜጊይስት በርሊን፣ በ2010 ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ጥቅም ላይ የዋለችው ኳስ ጃቡላኒ የሚል ስያሜ የተሰጣት ሲሆን በሴቶች ብቻ የተመረተ ስፒድ ሴል፣ የ2014 ቱ ብራዙካ እና የ2018 ቱ ቴልስታር ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም