የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ወጣቱ ትውልድ ባህሉን እንዲያውቅና ሀገራዊ አንድነቱን እንዲያጠናክር ዕድል ይፈጥራል - የበዓሉ ተሳታፊዎች

215

ዲላ (ኢዜአ) ህዳር 16/2015 የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ወጣቱ ትውልድ ብዝሃ ባህሉን እንዲያውቅና ሀገራዊ አንድነቱን እንዲያጠናክር ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የጌዴኦ ዞን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ተሳታፊዎች ገለጹ ።

17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን “ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን“ በሚል መሪ ሐሳብ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል የገደብ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ ዋቆ በዓሉ የብሔር ብሔረሰቦች የአብሮነትና የአንድነት መገለጫ ነው ብለዋል።

በዓሉን በዚህ መልኩ በተለያየ መርሃ ግብር ማክበር የብሔሮችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ወጣቱ ትውልድ ብዝሃ ባህሉን እንዲያውቅና ሀገራዊ አንድነቱን እንዲያጠናክር እድል የሚፈጥርለት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊ አንድነትና አብሮነት መጎልበት ለዘላቂ ሰላም ዋስትና መሆኑን ጠቅሰው ለጋራ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ለሀገራችን እድገት ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

የዲላ ከተማ ነዋሪ ወጣት ኢዮኤል ተሾመ በበኩሉ በዓሉ የእርስ በእርስ ትውውቅን በመፍጠር ወጣቱ ትውልድ ሀገሩን እንዲያውቅና ተፈጥሮአዊ ልዩነቶችን እንዲቀበል እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሷል።

ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቅሶ፤ በበዓሉ የተንጸባረቀውን ህብረብሔራዊ አንድነትና ወንድማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ልማት ማዋል እንደሚገባም ገልጿል።

የብሔር ብሔረሰቦች በዓል "የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ቀን ነው" ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ምስጋና ዋቄዮ ናቸው።

ህብር ብሔራዊ እንድነታችን እንዲናጠናከር ያስቻለ ነውም ብለዋል።

የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ በበኩላቸው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የህዝቦች የዘመናት የእኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ዋስትና ያገኘበት ቀን ነው ብለዋል።

በዓሉ የጋራ የሆኑ ሀገራዊ እሴቶችን እንዲጠናከሩና እንዲጎለብቱ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው በህዝቦች የነቃ ተሳትፎ እንዲሳኩ የሚፈለጉ የልማት ውጥኖችን በማነቃቃቱ ረገድ ድርሻው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የክልሉ ህዝቦች ለሀገራዊ አንድነት መጎልበትና ለዘላቂ ሰላም መስፈን ቅድሚያ በመስጠት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለ10 የዘማች ቤተሰቦች ለአንድ ወር የሚሆን የቀለብ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በስፖርታዊ ውድድሮችና በሌሎች መርሃ ግብሮች በዓሉ በድምቀት ተከብሯል ።

በበዓሉ ላይ የደቡብ ክልል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ፣ የብሄረሰቦች ምክር ቤት አፌ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም