የጡት ካንሰር ግንዛቤ መፍጠር አላማ ያደረገ የአምስት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ በጎንደር ከተማ ተካሄደ

169

ጎንደር ህዳር 18/2015(ኢዜአ)የጡት ካንሰር ግንዛቤ መፍጠር አላማ ያደረገ የአምስት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ በጎንደር ከተማ ተካሄደ።

ለሶስተኛ ጊዜ የተካሄደው የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ የእግር ጉዞ በዓለምፀሐይ የጡት ካንሰር ፋውንዴሽን አማካኝነት የተዘጋጀ ነው።

የፋውንዴሽኑ መስራች ዶክተር ፍሬሕይወት ደርሶ ድርጅቱ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር ስምምነት በመፈራረም በጡትና በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር የተጠቁ 4 ሺህ 800 የሚሆኑ ሴቶች ነጻ የመድሃኒት፣ መጠለያ፣ የምግብና የትራንስፖርት ወጪ እየሸፈነ ይገኛል ብለዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ሃኪም ዶክተር እዮኤል ነጋሽ ''በሆስፒታሉ ሕክምና ከሚደረግባቸው ከካንሰር ህመሞች መካከል የእናቶች የጡት ካንሰር የመጀመሪያውን ስፍራ እንደሚይዝ ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ባካሄደው ሳምንታዊ ነጻ የጡት ካንሰር ምርመራ ከተደረገላቸው 317 እናቶች 27ቱ የበሽታው ተጋላጭ ሆነው መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ በለጠ ፈንቴ የጡት ካንሰር በሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ስቃይና ሞት ለመቀነስ በጤና ተቋማት፤በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና በሀገር በቀል በጎ ፈቃደኞች የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ግለጸዋል።

የካንሰር ሕመም በማህበረሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ሰፊ የጤና ችግር ለመከላከል ሕብረሰተቡ የአመጋገብ ባህሉን ማስተካከልና አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ  ማድረግ አለበት ብለዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩ አቡሃይ ከተማ አስተዳደሩ ለዓለምፀሐይ የካንሰር ፋውንዴሽን የሕንጻ ግንባታ የሚውል ሁለት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በነጻ እንዲሰጥ መወሰኑንና በቅርቡ ቦታውን እንደሚያስረክብ ተናግረዋል።

እምስት ኪሎ ሜትር በሸፈነው የእግር ጉዞ ከጎንደር ከተማ የተለያዩ ቀበሌዎች የተውጣጡ ሴቶችን ጨምሮ የሕክምና ባለሙያዎችና የከተማው ሴት አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ጡት ካንሰር በዓለማችን በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር አይነቶች በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአብዛኛው ከ50 ዓመት በላይ በሆኑ ሴቶች ላይ የሚከሰት ቢሆንም በወጣት ሴቶች ላይም የመከሰት እድል እንዳለው ይገለጻል።

በየዓመቱ በመላው ዓለም 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ሴቶች ለጡት ካንሰር መጋለጣቸው በምርመራ እንደሚረጋገጥ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ 40 ሺህ ያህል ሰዎች በጡት ካንሰር ምክንያት እንደሚሞቱ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ለጡት ካንሰር አጋላጭ የሆኑ ነገሮችን ቀድሞ በመረዳት መከላከልና የህክምና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ የሕክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም