የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል 32 ሺህ ሜትሪክ ቶን የምግብ እህል ድጋፍ ተደራሽ ሆኗል--የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

231

አዲስ አበባ(ኢዜአ)ህዳር 18/2015 የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሃት ያደረጉትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ እስካሁን ወደ ትግራይ ክልል 32 ሺህ ሜትሪክ ቶን የምግብ እህልና ከ360 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተደራሽ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ተናገሩ።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መንግስት በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲያግዙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፌደራል መንግስትና ህወሃት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በዘላቂነት ለማቆም ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ መንግስት የትግራይ ክልልን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ሌሎች አካባቢዎችም የሰብዓዊ እርዳታን በስፋት ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም ( ዶ/ር ) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤  መንግስት የሰላም ስምምነቱን መሰረት በማድረግ ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል ያለ ገደብ ተደራሽ እንዲሆን እያደረገ ነው፡፡

በዚህም በአራት ኮሪደሮች በየብስ እንዲሁም በመቀሌና በሽሬ አውሮፕላን ማረፊያዎች በኩል እርዳታ ተደራሽ  እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ እስከ ህዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት  መንግስት በራሱ አቅም 13 ሺህ ሜትሪክ ቶን ጥራጥሬና አልሚ ምግብ ተደራሽ አድርጓል ብለዋል።

በእርዳታ ድርጅቶች በኩል ደግሞ 19 ሺህ ሜትሪክ ቶን የምግብ እህል ወደ ትግራይ ክልል ማሰራጨቱን ዶክተር ሽፈራው ገልጸዋል።

ባለፉት ሳምንታት ወደ ትግራይ ክልል የተላከው የሰብዓዊ እርዳታ ከ2 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።

ከምግብ አቅርቦት ባለፈም ትግራይ ክልልን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ እርዳታ ማጓጓዣ የሚውል ከ360 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ወደ አካባቢው ተልኳል ብለዋል።

መቀሌ የገባው ነዳጅም በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል ለአስፈላጊው ዓላማ ጥቅም ላይ እንደሚውል አንስተዋል።

መንግስት ከፍተኛ መድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ፣ ለትምህርት ቤቶችና ለአካባቢው ነዋሪ የውሃና ለንጽህና መጠበቂያ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የሰብዓዊ ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡት ኮሚሽነሩ፤ ለዚህም ከአጋር አካላትና ከዜጎች ጋር በቅንጅት እተየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በነበረው ግጭት የጉዳት ሰለባ የሆኑ ወገኖችን በማገዝ መንግስት እያደረገ ካለው ጥረት ባለፈ የማህበረሰቡም ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይሄው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በጦርነቱ ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን ወደ ቀያቸው በመመለስ በዘላቂነት ለማቋቋም መንግስት አስተባባሪ ኮሚቴ አደራጅቶ እየሰራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

መደበኛ አገልግሎቶችን ከማስጀመር ጎን ለጎን ዜጎች ወደ መደበኛ ህይወታቸው እስኪመለሱ ድረስ ሰብዓዊ ድጋፉን አጠናከሮ ለመቀጠልም በቂ ዝግጅት ማድረጉን ነው የተናገሩት።

መንግስት ሀብት የማሰባሰብና የእርዳታ ድርጅቶችን አቅም ለመጠቀም እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንደያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም