ቀጥታ፡

መስቀል የዕምቅ ባሕላዊ ትውፊቶች ዓውደ ርዕይ-የበዓሉ ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ መስከረም 17/2011 መስከረም 16 አመሻሽ፤ በመስቀል ክብረ በዓል ዋዜማ፣ በዕለተ ደመራ በመስቀል አደባባይ ለታደመ እንግዳ ዕልፍ ትዕይንቶችን ይታዘባል። የኢትዮጵያዊያን ውበት፣ ጥንታዊ ትውፊቶች፣ አገር በቀል የማንነት መገለጫዎች፣ የአብሮነትና አንድነት ድንቅ ምስጢር ይደነቃል። አለፍ ሲልም በኢትዮጵያ ታሪካዊና ባሕላዊ ሀብቶችን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አገራዊ ትውፊቶችን፣ የአለባበስ ስነ ስርዓቶችን፣ ፍልስፍናና ዕውቀቶችን፣ ተዳሳሽና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብ፣ በመገልገልና ለትውልድ በመዘከር ረገድ ያላትን የማይተመን ሚና ይገነዘባል። የበዓሉ ታዳሚዎች በዓለም የማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት የተመዘገበው መስቀልና መሰል የአደባባይ ክብረ በዓላት ለኢትዮጵያ ባሕላዊና ታሪካዊ ዕምቅ ሃብቶችና ቅርሶች ለዓለም ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ የቱሪዝም ዓውደ ርዕይ ናቸው ይላሉ። ዲያቆን ዮሴፍ ከተማ ከጥንት ጀምሮ በዜማ መሳሪያነት ሲያገለግል የቆየው 'በገና' ተብሎ የሚጠራው የክር የዜማ መሳሪያ ይዞ ነው ያገኘነው። 'በገና ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያኗን አስተምህሮና ትውፊቷን የምታሳይበት ጥንታዊ መሳሪያ ነው' የሚለው ዮሴፍ፤ ቤተ ክርስቲያኗ ዓለማዊ የሙዚቃ ጠበብት ባልነበሩበት ከሺህ ዓመታት በፊት በረቀቀና በመጠቀ ዜማና ዝማሬ የምትገለገልበት መሳሪያ እንደሆነ ይገልጻል። እናም በደመራና በሌሎች የአደባባይ ክብረ በዓላት አያሌ የአልበሳት፣ የስዕል ጥበብና የቅርስ ሀብቶች ማሳያ 'ዓውደ ርዕይ' ናቸው ይላል። በተመሳሳይ ወጣት ፍጹም ግሩምና አቶ ሲሳይ ደምሴ ዛሬ ላይ በአገልግሎት በብዛት የማይታየውን መለከትና ነጋሪት በመያዝ ትርዒት ሲያሳዩ ተመልክተናል። በመለከትና ነጋሪት ቤተ ክስርስቲያኗ ለመንፈሳዊ አገልግሎት፣ ነገስታት ደግሞ ለአዋጅና ለጦርነት መቀስቀሻ፣ ለደስታ ቀን መግለጫ፣ ለጉዞ ማጀቢያና ሌሎች ማኅበራዊ ተግባራት ሲገለገሉበት የነበሩ ጥንታዊ የዜማ ዕቃዎች እንደሆኑ ይጠቅሳሉ። መለከት አክሱም በአንድ አባት ብቻ ሲገለገሉበት እንደነበር የሚጠቅሰው ፍጹም፤ አሁን ላይ ማሳሪያው እንዳይጠፋ በመማርና በማስተዋወቅ እንደሚገኙ ገልጾ፣ በአደባባይ መሳሪያዎቹን ማስተዋወቅ ለቱሪዘም ዘርፉ እድገት የራሱ ፋይዳ አንደሚኖረው ጠቅሷል። ወጣት ሮማን ቅዱሳን ደግሞ ቤተክርስቲያኗ ለዘመናት ዛሬም ላይ የምትገለገልበት በዓለማዊ ሙዚቃም አገልግሎት ላይ የሚገኘውን ከበሮ እየመታች ነበር። ከበሮ የወረብ፣ የዝማሜ፣ የዝማሬና ሌሎች እንደየምስጋና ዐውዱ የአጨዋወት ስርዓቶች እንዳሉት የምትገልጸው ሮማን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ ክራር፣ ከበሮ፣ በገና መሰል የዜማ መሳሪዎች በመገልገል፣ በመጠበቅና በማስተዋወቅ ቤተ ክርስቲያን የሚስተካከላት እንደሌለ ትገልጻለች። ወጣት ሌሊሳ ግዛው ደግሞ በኢትዮጵያ አገር በቀል ስርዓተ ትምህርት ወይም የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪ ሲሆን ከአያሌ ዘመናት በገጠራማ የአገሪቷ ክፍሎች የአብነት ደቀ መዛምርት የሚለብሱትን አለባበስ ለብሶ ነው በደመራ በዓል ላይ የተገኘው። እንዲሁም አቶ አለማየሁ ብርሃኑ በጃኖ ባህላዊ ልብስ፣ ወጣት ሲሳይ ደግሞ ራሱ በሰራው ግንጉዛ ተብሎ በሚጠራው የጋሞ ብሔረሰብ ባሕላዊ አለባበስ ተውቦ ነው የወጣው። የደመራ ክብረ በዓል በኢትዮጵያ ከሚከበሩ የአደባባይ ኃይማኖታዊና ትውፊታዊ በዓላት መካከል በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ የመጀመሪያው ደማቅ ክብረ በዓል ነው።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም