የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት በክልሉ በዓመት እስከ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት በክልሉ በዓመት እስከ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ
ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 በአማራ ክልል የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት በዓመት እስከ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት እንደሚሰጡ የክልሉ ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት አደራጅ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ሽታሁን ይርሳው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል እያሳደጉ ለኢንቨስትመንት እድገት እገዛ እያደረጉ ነው።
በክልሉ በገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት የተደራጁ አንድ ሚሊዮን ያህል አባላት መኖራቸውን ገልጸው፤ በ3 ሺህ 734 የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት፣ ዩኔኖችና ፌዴሬሽን በገጠርና በከተማ መደራጀታቸውን ተናግረዋል።
የማህበር አባላቱ 4 ቢሊዮን ብር ቁጠባ ያሰባሰቡ ሲሆን በዓመት ለአባሎቻቸው እስከ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ብድር በመስጠት የብድር አቅርቦት ችግርን እያቃለሉ እንደሆነ ተናግረዋል።
አባላቱ በአነስተኛ ወለድ በየጊዜው በሚወስዱት ብድር በገጠር በግብርና ግብዓት አቅርቦት፣ በእንስሳት ማድለብና እርባታ ዘርፍ በመሰማራት የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን እንዲሁም በከተማ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ በንግድና ትራንስፖርት ዘርፍ በመሰማራት ኢኮኖሚያቸውን እያሳደጉ እንዲመጡ ማስቻሉንም ገልፀዋል።
የቀንዲል ገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር የስራ አመራር ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሞኘ መንግስቴ በበኩላቸው ማህበሩ በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ በ50 የመንግስት ተቋማት የሚሰሩ 2 ሺህ 200 ሰራተኞችን በአባልነት አቅፎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ማህበሩ ካፒታሉን 100 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው፤ ለአባላቱ እንደ ቁጠባና መክፈል አቅማቸው እስከ 800 ሺህ ብር ድረስ ብድር እየሰጠ ነው ብለዋል።
አባላቱ በአነስተኛ ወለድ ወስደው ቤት በመስራት የቤት ባለቤት ከመሆን ባለፈ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች በመሰማራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረጋቸው እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በቀጣይም ማህበሩ የተለያዩ ቅርንጫፎችን ከፍቶ በኔት ወርክ በማያያዝ ወደ ማይክሮ ፋይናንስ ለማደግ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የቀንዲል የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር አባል የሆኑት ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ገድፍ እና አቶ ፈንታሁን አመሸ የማህበሩ አባል በመሆን ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለያየ ጊዜ ብድር በመውሰድ ቤት መስራትን ጨምሮ የተለያዩ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ ስራዎችን መስራት መቻላቸውን ተናግረዋል።