ቀጥታ፡

አራተኛው 'የአፍሪካ ሶርቲንግና ፋሽን' አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ መስከረም 17/2011 ከ250 በላይ ዓለም አቀፍ አምራቾችና  ከመላው ዓለም የተውጣጡ 4 ሺህ ነጋዴዎች የሚሳተፉበት አራተኛው 'የአፍሪካ ሶርቲንግና ፋሽን' አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ  ሊካሄድ ነው። የአውደ ርዕዩን መካሄድ አስመልክቶ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ዛሬ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ አውደ ርዕዩ በዋናነት የጥጥ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የአልባሳት፣ የቆዳ ውጤቶች፣ የቤት ውስጥ ማሳመሪና የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ውጤቶች ይቀርባሉ። በአገሪቷ በቀላል የማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ያለውን አንቅስቃሴ ከፍ ለማድረግም  አውደ ርዕይ መዘጋጀቱ ጠቃሚ ነው ብለዋል። ''የአፍሪካ የሶርቲንግና ፋሽን'' ሳምንት ብቸኛው የአህጉሪቱ የቴክኖሎጂ የንግድ ትርኢት በመሆኑ ከ25 የሚበልጡ አፍሪካዊያን ዲዛይነሮች ከዓለም አቀፍ ሸማቾችና የፋሽን ብራንድ አቅራቢዎች ጋር  ትስስር የሚፈጥሩበት መድረክም ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ጎሹ ነጋሽ በበኩላቸው፣ አሁን የተጀመረው መሰል አውደ ርዕይ አገሪቷ በዘርፉ እያስመዘገበች ያለውን ውጤት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደረስ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል ብለዋል። በአውደ ርዕዩ ከ12 የሚበልጡ የደቡብ አፍሪካ የቆዳ ውጤቶች አምራቾች ታዋቂ ዓለም አቀፍ የፋሽን አቅራቢዎችና ሸማቾች ለእይታ ይቀርባሉ። አውደ ርዕዩ  መሪ ቃሎቹም "በምርት ዘላቂነት መፍጠር እና ትራንስፎርሚሽን በቴክኖሎጂ" የሚሉ ናቸው። እ.አ.አ በ2017 ከተካሄደው ተመሳሳይ አውደ ርዕይ አንጻር ሲታይ ፣የአቅራቢዎች ቁጥር 30 በመቶ ፣ የሚጠበቀው የጎብኚዎች ቁጥር ደግሞ 5 በመቶ ከፍ እንዳለም ተገልጿል። ከአፍሪካ አገራት ባሻገር በአውደ ርዕዩ፣ ከእሲያ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከአውሮፓ አገራት ተሳታፊዎች መኖራቸውም ተገልጿል። አውደ ርዕዩ   ከመስከረም 21 እስከ 24/2011 ድረስ እንደሚካሄድ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም