ሴቶች በስራ ቦታ ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ ውጤታማ ስራ እንዲሰሩ ከማስቻል አንፃር ክፍተቶች አሉ- የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

141

አዳማ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 ሴቶች በስራ ቦታ ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ ውጤታማ ስራ እንዲሰሩ ከማስቻል አንፃር ክፍተቶች መኖራቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ይህን ያለው በሴቶች የስራ ቦታ ግኑኝነት፣ ተሳትፎና እኩል ተጠቃሚነት ዙሪያ ከዓለም የስራ ድርጅት ጋር በመሆን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት በአዳማ ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ነው።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢንዱስትሪዎችም ሆነ በህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሴቶችና ወጣቶች የስራ ቦታ ውጤታማነት የሚያረጋግጡ ደረጃዎች ያልተሟሉ መሆኑን እየተመለከትን ነው ብለዋል።

የመድረኩ ዓላማ የስራ ቦታ ደረጃ አጠባበቅ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላት አመራሮች በቂ ግንዛቤ አግኝተው በቀጣይነት ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲያግዙ ለማስቻል ነው።

በተለይ በሴቶች በስራ ቦታ ላይ የሚደርስ ተፅእኖ ፣የእኩል ክፊያ ያለማግኘት፣ የወሊድ ፍቃድ በአግባቡ ያለመጠቀምና ፆታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ በጉዳዩ ዙሪያ በቅንጅት ለመስራት እንደሆነም ዶክተር ኤርጎጌ ገልጸዋል።

በስራ ቦታ በሴቶች ላይ በሚደርሰው አድሎአዊ አሰራርና ጥቃት የአምራች ተቋማት ላይም ሆነ የሀገር ልማትና እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በተለይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስመንት ላይ ለመሰማራት የሚመጡ ድርጅቶችና ተቋማት እንደ መስፈርት ከሚጠይቋቸው ጉዳዮች መካከል የስራ ስብጥርና ደረጃ መጠበቁ፣ ደህንነትና ውጤታማነት መሆኑን ሚኒስትሯ  አመልክተዋል።

በሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የተመረጡ የልማት ድርጅቶች የስርዓተ ፆታ አካቶ ትግበራ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ ሚኒስቴሩ በ36 ተቋማት ላይ ጥናት ማካሄዱንና በስራ ቦታ እኩልነት ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን አሳይቷል ብለዋል።

ችግሮቹን በጋራ ለመቅረፍ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና አመራሮች አስፈፃሚ አካላት የስራ ቦታ ህጎችን ጨምሮ የስርዓተ ፆታ አካቶ ትግበራ ጉዳይ በትክክል መተግበሩን በክትትልና ቁጥጥር ወቅት እንዲቃኙት የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ በሚል መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ሚስስ ካቲሪና ሱዚ እንደገለፁት በኢትዮጵያ የስርዓተ ፆታ እኩልነት መረጋገጥ በምርትና ምርታማነት ላይ የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ የስርዓተ ፆታ እኩልነት በስራ ቦታ ማረጋገጥ በተለይ ኢትዮጵያ ለመተግበር የፈረመቻቸው የስራ ቦታ ደህንነት ህጎች ተፈፃሚነት ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የሴቶች ኮከስ በቅንጅት እንዲሰሩ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሆነም ገልጸዋል።

በተለይ በስራ ቦታ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት፣ አድሎና ፍትሃዊነት የጎደለው አሰራር በምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ መኖሩን ጠቁመዋል።

ከጠቅላላ የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰው ፍትሃዊ የስራ እድሎችን እኩል መዘርጋት ለሀገሪቱ ልማትና እድገት መፋጠን ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም