ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሶማሌ ክልል 110 የውሃ ፓምፖችን ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሶማሌ ክልል 110 የውሃ ፓምፖችን ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ በሶማሌ ክልል ደረጃ በተካሄደው የሌማት ትሩፋት ማስተዋወቂያ መርሃ-ግብር ላይ በመገኘት አስረክበዋል።

እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል የምናደርገው ብርቱ ጥረት አካል የሆነው የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ በዛሬው እለት በሶማሌ ክልል በይፋ በወተት ምርት፣ በዶሮና በማር ምርት ማሻሻያ ፕሮግራሞች በይፋ ማስጀመራቸውን የገለጹት ከንቲባዋ አስተዳደሩም 110 ያህል የውሀ ፓምፖችን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ምስራቅ በር ጠንካራ ደጀን የሆነው የሶማሌ ክልል ህዝብና መንግስት አሁንም ኢትዮጵያን በሌማት ትሩፋት ገበታዋን ለማትረፍረፍ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም የክልሉን ፀጋዎች ማዕከል በማድረግ የሃገር ሉአላዊነትን በማስከበር ረገድ እንዳሳየው ጀግንነት በሌማቱም ግንባር ታላቅ ስኬት እንደሚያሳየን እምነታችን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በእርግጥም ያለውን የተፈጥሮ ፀጋና አቅም በትክክል መጠቀም ከተቻለ ክልሉ መላውን ኢትዮጵያ የመመገብ አቅም አለውም ብለዋል፡፡

“በተለይም የወተት ምርት በማትረፍረፍ ለሃገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ ለሌሎችም የምንተርፍ ህዝቦች እንሆናለን” ያሉት ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩ የክልሉ ፕሮግራም እንዲጠናከር የመስኖ ውሃ ልማት የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴው ውጤታማ እንዲሆን ቀጣይ ድጋፍ እንደሚያደርግም አክለዋል።

ከዚህም ባሻገር ከተማችን ለክልሉ አርሶና አርብቶ አደሮች ምርቶች ገበያ እንድትሆን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ የምናደርግ ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም