ከ592 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አዳንኩ አለ---የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
ከ592 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አዳንኩ አለ---የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን
አዳማ መስከረም 17/2011 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ወጪ ቆጣቢ የአሰራር ሥርዓትን በመዘርጋት ከ592 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ። የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ኃይለመስቀል ተፈራ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ኮርፖሬሽኑ ከመንግሥት የሚረከባቸውን የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን አዋጪና ወጪ ቆጣቢ በሆነ አሰራር በማከናወን ወጪውን አድኗል። በተለይም በመሠረተ ልማት ፕሮጄክቶች ግንባታ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል። ለዚህም ኮርፖሬሽኑ የካይዘን የአሰራርና የአመራር ፍልስፍናን መተግበሩና የሠራተኞችና ሙያተኞች የአንድ ለአምስት ልማት ቡድን አደረጃጀት ወሳኝ ሚና ነበራቸው ብለዋል። በበጀት ዓመቱ ከ360 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ለማዳን አቅዶ ወደ ሥራ የገባ ቢሆንም፤ አመራሩና ሠራተኛው በቅንጅት ባደረገው ርብርብ ከዕቅዱ በላይ ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል። የአገልግሎት ጊዜያቸው ያበቁና ያረጁ ሎደሮች፣ግሬደሮችና ተሽከርካሪዎችን በራሱ አቅም አድሶ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል የመስኖ ግድቦች፣የስኳር ፋብሪካዎች የመስኖ ካናሎች ግንባታ፣በመንገድ ልማትና ጥገና ዙሪያ የተከናወኑ ሥራዎችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ አሰራር መዋላቸውን አመልክተዋል። የመንገድ ግንባታና ጥገና፣የድልድዮችና የአየር ማረፊያዎችን ግንባታ በወጪ ቆጣቢ አሰራር በማከናወን አበረታች አፈፃፀም እንደታየበት የገለፁት ደግሞ በኮርፖሬሽኑ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ የምህንዲስና ሥራዎች ዋና መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን በጅጋ ናቸው። በአዳዲስ ፕሮጄክቶች ግንባታ ላይ የአሰራር አዋጭነት ጥናት ከማካሄድ ባለፈ ጥገና በሚከናወንባቸው ፕሮጄክቶች ላይ ወጪ ቆጣቢ ሥራዎችን ለመፈፀም ለሰው ኃይሉ ሙያዊና የአቅም ግንባታ ስልጠና ተከታታይነት ባለው መልኩ እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።