የኢሉባቦር ዞን ማረሚያ ቤት በሕግ ታራሚዎች ላይ ከሚሰራው የማረም ስራ በተጓዳኝ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል

84

መቱ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 ማረሚያ ቤቱ ከፀባይ ማረም ስራ ጎን ለጎን በተለያዩ የግብርና መስኮች መልካም ተሞክሮ የሚሆኑ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የኢሉባቦር ዞን ማረሚያ ቤት አስታወቀ።

በማረሚያ ቤቱ ባለው መሬት ላይ በተለይ በግብርና ዘርፍ ለአከባቢዉ ማህበረሰብ እንደ ሰርቶ ማሳያና መልካም ተሞክሮ የሚሆኑ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱራህማን አብደላና የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ የተመራ ቡድን በማረሚያ ቤቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ምልከታ አድርጓል።

የማረሚያ ቤቱ ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ተናኜ ወልዱ የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤቱ ቆይታቸው ፀባያቸውን ከማነፅ በተጨማሪ ወደ ማህበረሰቡ ሲመለሱ ባላቸው መሬት ላይ እንዴትና ምን ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ ልምድና ዕውቀት የሚቀስሙበት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ባሻገር የአከባቢው ማህበረሰብ በአትክልት፣ በፍራፍሬ፣ በሩዝ፣ በአረንጓዴ ልማትና በመሳሰሉት ስራዎች ላይ መልካም ልምዶችን ሊቀስምበት የሚችል ትልቅ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ "የማረሚያ ቤቱ ስራዎች የከተማ ግብርናን ለማስፋፋትና በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውጤታማ የልማት ስራዎችን መስራት እንደሚቻል ምሳሌ እየሆነ ይገኛል" ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የገጠር ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አብዱራህማን አብደላ ማረሚያ ቤቱ የግብርና ምርምርና የሙያ ማሰልጠኛ ተደርጎ ሊወሰድ የሚያስችለውን ትልቅ ስራ እያከናወነ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

መንግስት የቀረፃቸውን ዕቅዶች በተቀናጀ መልኩ በተግባር ማየት የሚቻልበትና የአከባቢው ማኅበረሰብ ልምድ ሊቀስምበት የሚገባ መሆኑንም አመልክተዋል።

በክልሉ የሚገኙ ሌሎች ማረሚያ ቤቶች፣ የግብርና ምርምር ማዕከላት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች የምርምር ስራን የሚያከናውኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ልምዱን ሊቀስሙበት ይገባል በማለት ተናግረዋል።

በተለይ የመንግስትን ወጪ ሳይጠይቁ በውስጥ አቅማቸው ይህን አርአያነት ያለው ስራ መስራታቸው ለሌሎችም ተሞክሮ ሊሆናቸው እንደሚገባ አክለዋል።

ማረሚያ ቤቱ ከአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ከሩዝ ምርት ስራ በተጨማሪ የአረንጓዴ ልማት ስራ እና ሰው ሰራሽ ሐይቅን በመስራትም የመዝናኛ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም