የምግብ መድሃኒትና ህክምና መሣሪያዎች የደህንነትና ጥራት ቁጥጥር ማዕከል በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ሊገነባ ነው

172

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የምግብ መድሃኒትና ህክምና መሣሪያዎች የደህንነትና ጥራት ቁጥጥር ማዕከል ግንባታ ተጀመረ።

የግንባታው ባለቤት የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ሲሆን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ግንባታውን በይፋ አስጀምረዋል።

ዶክተር ሊያ ታደሰ በግንባታ ማስጀመሪያው ላይ እንደተናገሩት ማዕከሉ የዜጎቻችንን ጤና ለመጠበቅና በጥራት መጓደል ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉትን የጤና ጉዳቶችና ሞትን ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው ።

በተጨማሪም በቀጣይ ዓመታት በጤናው ዘርፍ የደህንነትና ጥራት ቁጥጥር ስርዓቱን በማዘመን ዓለም አቀፍ ደረጃውን ለማስጠበቅ የተቀመጠውን ግብ የማሳካት ሚናው ከፍተኛ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ በ7ሺህ 650 ካሬ ሜትር ላይ የሚገነባ ሲሆን የጥራት ምርመራ የሚደረግባቸው 257 ክፍሎች እንደሚኖሩትም ተጠቁሟል፡፡

ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በቂ ኃይል አቅርቦት እንዲሁም የማህበረሰብ ጤናን ከግምት ያስገባ ዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት እንደሚኖረውም ተጠቅሷል፡፡

ከዓለም ባንክ በተገኘ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚገነባ ማዕከሉ በአንድ ጊዜ 400 ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚያስችል ስፍራና በአንድ ጊዜ ለ1 ሺህ ሰራተኞች መመገቢያ የሚሆን አዳራሽ ይኖረዋልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በበኩላቸው ማዕከሉ ለዘርፉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረው ለግንባታው መጀመር አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ማዕከሉ የሚገነባው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሲሆን በዕለቱም ግንባታውን ከሚያከናውነው የኮንስትራክሽን ተቋራጭ ድርጅት ጋር የፊርማ ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡

በተያያዘም በዕለቱ ለሁሉም ክልሎች የምግብ መድሃኒትና መሣሪያዎች ጥራት ቁጥጥር ተቋማት አንድ አንድ የስራ ተሽከርካሪ እንደተበረከተላቸው ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም