በትግራይ ክልል ከሽራሮ እስከ አድዋ በመጀመሪያው ዙር ለ450 ሺህ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ቀርቧል - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ከሽራሮ እስከ አድዋ በመጀመሪያው ዙር ለ450 ሺህ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ቀርቧል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 በትግራይ ክልል ከሽራሮ እስከ አድዋ በመጀመሪያው ዙር ለ450 ሺህ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረቡን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
በመንግሥትና ህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በኬኒያ ቀጣይ ውይይት በማድረግም ለስምምነቱ ገቢራዊነት ፊርማቸውን ማኖራቸው ይታወሳል።
በዚህም መሰረት መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ያለ ገደብ እንዲገባ አራቱን የየብስ ኮሪደሮችና የአየር ትራንስፖርት ለሁሉም ክፍት በማድረግ ድጋፉ ተደራሽ እንዲሆን በመሥራት ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የድጋፉ ጊዜያዊ አስተባባሪ ዘሪሁን ዘውዴ፤ በመንግሥት በኩል በትግራይ ክልል በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ከሽራሮ ጀምሮ አዲ ሀገራይ፣ አዲ ነብሪ፣ ሽሬ፣ ሰለክለካ፣ አክሱምና አድዋ ድረስ በሁሉም አካባቢዎች ያልተቋረጠ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም በመጀመሪያው ዙር ብቻ ከ450 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ከ90 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴና አልሚ ምግብ ተሰራጭቷል ነው ያሉት።
በእነዚህ አካባቢዎች ከህፃናት እስከ አዋቂ የሚያስፈልጋቸው ምግብ ነክና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች እየቀረቡ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ ሰብኣዊ ድጋፍ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች በየጣቢያው ገብተው ለሕብረተሰቡ እየተከፋፈለ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል በ70 መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን ተደራሽ ለማድረግም ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለተፈናቃዮች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ በስፋት እናቀርባለን ብለዋል።
በክልሉ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ለጋሽ ድርጅቶች በሕጋዊ መንገድ ድጋፍ ለማድረስ በሚንቀሳቀሱበት ጉዳይ ላይ መግባባት ላይ ደርሰናል ነው ያሉት።
በዚህም መሰረት በምግብ አቅርቦት፣ በመድኃኒትና ሕክምና ቁሳቁስ እንዲሁም በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ እንቅስቃሴ ጀምረዋል ብለዋል።