ቀጥታ፡

የህዝቦች ትስስር በወቅታዊ ችግር ፈተና ላይ እንዳይወድቅ ምዕመናን ሰላምን ሊያስጠብቁ ይገባል--- ሊቀ ዻዻስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ

አዳማ/ጅማ መስከረም 17/2011 የህዝቦች ትስስር በወቅታዊ ችግር ፈተና ላይ እንዳይወድቅ ሁሉም ምዕመናን የአገሩን ሰላም ሊጠብቅ እንደሚገባ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብክት ሊቀ ዻዻስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አስታወቁ። በተመሳሳይ እምነቶቻችንን በመጠበቅ በጋራ ጉዳዮች ላይ ተደምረን አገራችንን ታላቅ ልናደርጋት ይገባ" ሲሉ የጅማ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ አስገንዝበዋል ። የደመራ በዓል በአዳማና በጅማ ከተሞች በድምቀት ተከብሯል። የምስራቅ ሸዋ ዞን ሊቀ ዻዻስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የደመራ በዓል በአዳማ መስቀል አደባባይ በድምቀት በተከበረበት ወቅት እንዳሉት ሁሉም ምዕመናን የመስቀል በዓልን ሲያከበር የመስቀል መገለጫ በሆነው በፍቅርና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል። "በዓሉ ሲከበር በመስቀሉ የተገለጸውን ድንቅ የእግዚአብሄር ፍቅር በተግባር ለመኖር እየሞከርን ሌሎችም ይህ ፍቅር እንዲደርሳቸው የምንችለውን ሁሉ እያደርግን ሊሆን ይገባል"  ብለዋል። " ካለሰላም እምነትንም ሆነ ማንኛውንም ጉዳይ መፈጸም አይቻልም " ያሉት አቡነ ጎርጎሪዮስ በተለይ የህዝቦች ትስስር በወቅታዊ ችግር ፈተና ላይ እንዳይወድቅ ሁሉም ምዕመን የአገሩን ሰላም ተግቶ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል። ቤተ ክርስቲያኗ ለረዥም ዓመታት በህዝቦች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር ስትሰራ መቆየቷን አስታውሰው "ይህንን ተግቧሯን አጠናክራ ትቀጥላለች" ብለዋል። የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ ለተከታዩ ትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ከምታደርገው ጥረት ጎን ለጎን መንግስትና የእምነቱ ተከታዮች የድርሻቸውን እንዲወጡም ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አሳስበዋል። የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ በበኩላቸው የደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ ባሻገር ለአገር ገጽታ ግንባታና ለቱሪዝም ልማት እድገት የጎላ ሚና እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል። "የዘንድሮው የደመራ በዓል በቤተክርስቲያኗ ለሁለት ተከፍሎ የነበረው ሲኖዶስ እርቀ ሰላም በማውረድ ዳግም ወደ አንድነት በተመለሰበት ወቅት ላይ መከበሩ ልዩና ታሪካዊ ያደርገዋል" ብለዋል። የበዓሉ ታዳሚ አቶ ግርማ እየሱስ በሰጡት አስተያየት "መስቀልን ስናስብ በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በመሰቀል ላይ ተሰቅሎ የተቀበለውን ከባድ መከራ በማስታወስ ሊሆን ይጋባል" ብለዋል። አሁን የሚስተዋለውን የገሀዱን አለም ተግዳሮት በአሸናፊነት ለመወጣት እግዚአብሔር ትዕግስትንና ፅናትን እንዲሰጥ ተግቶ መፀለይ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በተመሳሳይ በአሉ በጅማ ከተማ በተከበረበት ወቅት በእንግድነት የተገኙት የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ "እምነቶቻችንን ጠብቀንና በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተደምረን በአንድነት መንፈስ አገራችንን ወደፊት ማራመድ ይጠበቅብና" ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል ። የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ ሙሃመድ በበኩላቸው የዘንድሮ የደመራ በአል ለረዥም ጊዜ ተለያይተው የነበሩ ሲኖዶሶች አንድ በሆኑበት ጊዜ በደመቀ ሁኔታ መከበሩ የተለየ እንደሚያደርገው ተናግረዋል ። እንደ ከንቲባው ገለጻ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች በአሉን ሲያከብሩ በሃይማነት ሽፋን የአካባቢውንና የሀገርን ሰላም ለማደፍረስ የሚደረግ ማንኛውንም እንቅስቃሴ በጽናት በመመከት መሆን አለበት። ከእዚህ በተጨማሪ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ያላቸውን አንድነት የበለጠ በሚያጠናክሩበት መልኩ በዓሉን እንዲያከብሩም አስገንዝበዋል። ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ሩት ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት "የመስቀልን በዓል ስናከብር ከሌሎች የእምነቱ ተከታዮች ጋር ያለንን አንድነትና መተሳሰብ በማጎልበት ነው" ብለዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም