ቀጥታ፡

አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኢትዮጵያን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ እንዲያስገኝ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን

ጅማ (ኢዜአ) ህዳር 16 ቀን 2015 አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኢትዮጵያን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ እንዲያስገኝ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የተሳታፊዎች መለያና አጀንዳ ማሰባሰብን የተመለከተ ውይይት በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች የተውጣጡ አባገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች በውይይቱ ተሳትፈዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የወሊሶ ከተማ አባ ገዳ ተስፋዬ ቱጆ ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት በመሆኗ ኢትዮጵያውያንም ችግራቸውን በምክክርና በውይይት ለመፍታት የሚያዳግታቸው ሕዝቦች አይደሉም ብለዋል።

''ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ያሉብንን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ችግሮች በምክክር እንዲፈቱ የጀመረው ጥረት ሊያጠናክር ይገባል'' ሲሉም ገልጸዋል።

''የትኛውም አለመግባባትና ቅራኔን በመነጋገር ስንፈታ የኖርን ህዝቦች ነን፤ የምክክር ኮሚሽኑም ይህን ሀላፊነት እንዲወጣ ድጋፍ እናደርጋለን'' ብለዋል።

ቄስ ታከለ ዳዲ በሰጡት አስትያየት የምክክር ኮሚሽኑ በአገሪቷ ያሉ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦችንና የተዛቡ ትርክቶችን ለማስተካከል ትልቅ እድል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሂደቱ እንዲሳካም በሚችሉት ሁሉ እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረው በአገሪቷ የተሟላ ሰላም እንደሚመጣ ተሰፋ እንዳላቸው አመላክተዋል።

አቶ አሸብር ታደሰ ''እንደ ሀገር የገጠሙን ችግሮች በሰላም እና በመነጋገር ለመፍታት ሁላችንም መተባበር አለብን'' ብለዋል።

አብዛኛው የኢትዮጵያ ችግሮች መነሻቸው ፖለቲካዊ ፍላጐትና የተዛቡ ትርክቶች መሆናቸውን ገልጸው፤ ኮሚሽኑ እነዚህ የተራራቀ አስተሳሰብ ያላቸውን አካላት ማቀራረብ ላይ ማተኮር አለበት ሲሉ መክረዋል።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው ኮሚሽኑ በአገሪቷ በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈጠሩ ችግሮችና አለመግባባቶች መፍትሔ የሚያስገኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአገራዊ ምክክሩ ሊነሱ የሚገባቸውን አጀንዳዎች እና ጥያቄዎች በማሰባሰብ ግብአት እንዲሆኑ እገዛ ማድረግ እንዳለበትም ጠይቀዋል።

ከምንም በላይ አሁን በኢትዮጵያ በተለያየ መልኩ የሚስተዋሉትን ልዩነቶች ማጥበብ የሚቻለው በምክክር ብቻ እንደሆነ ሁሉም ማመን እንዳለበትም ገልጸዋል።

ዜጎች የየአካባቢያቸውን ተጨባጭ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን ማቅረብ እንዳለባቸውም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም