ለስምምነቱ ስኬታማነት ሁሉም ሊተጋ ይገባል-የትግራይ ክልል ተወላጆች - ኢዜአ አማርኛ
ለስምምነቱ ስኬታማነት ሁሉም ሊተጋ ይገባል-የትግራይ ክልል ተወላጆች
ደብረ ብርሃን (ኢዜአ) ህዳር 17 /2015 በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ሀገራዊ አንድነትን አጠናክሮ ማስቀጠል የሚያስችል በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም ሊተጋ ይገባል ሲሉ በደብረ ብርሃን ከተማ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ።
ከክልሉ ተወላጆች መካከል ወይዘሮ ምህረት አሰፋ ለኢዜአ እንደገለፁት በነበረው ጦርነት የሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ የንብረት ውድመት ደርሷል።
"በተለይ በነበረው ጦርነት ዋነኛ ተጋላጭ የሆኑ ወንድማማችና እህትማማች ህዝቦች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ ሃብትና ንብረታቸው ወድሟል" ብለዋል።
አሁን ላይ በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት ጦርነቱ በመቆሙ ተጨማሪ የሰው ህይወት እንዳይጠፋና ንብረት እንዳይወድም ማድረጉን ተናግረዋል።
በተለይም በነበረው ጦርነት ቀጥተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ህዝቦች እፎይታን የሰጠ ከመሆኑም ባለፈ ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ አንድነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም ሊተጋ እንደሚገባ አመልክተዋል።
"የሰላም ስምምነቱ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እፎይታ የሰጠና በተለይም የትግራይ ክልልን ጨምሮ በጦርነቱ በቀጥታ ተጎጂ የነበሩ ህዝቦችን ከዘርፈ ብዙ ችግር የሚታደግ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ብርሃን ህይወት ካሳ ናቸው።
"ከጦርነት ውድመት እንጂ ትርፍ አይገኝም" ያሉት አቶ ብርሃን መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀርብ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
በብዙ ልፋትና ትዕግስት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም በማስተዋል መጓዝ እንደሚገባው አመልክተዋል።
ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚፈልጉ አንዳንድ አካላት እያራመዱ ካለው ጦርነት ቀስቃሽ መልዕክቶችና መሰል ተግባራት በመቆጠብ ለሰላም ዘብ መቆም ላይ አተኩረው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ወይዘሮ አዜብ ወልደስላሴ በበኩላቸው የተደረሰው የሰላም ስምምነት እፎይታን የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የሰላም ስምምነቱን ጥላሸት ለመቀባት እየተንቀሳቀሱ ያሉ አንዳንድ አካላትም ከአጥፊ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
"አሁን ላይ የትግራይ ክልል ህዝብም ሆነ መላው ኢትዮጵያዊ የሚያስፈልገው ልማትና እድገት እንጂ ጦርነት ባለመሆኑ የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዲሆን ሁሉም ማገዝ ይገባዋል" ሲሉ አመልክተዋል።
የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ከማድረግ ጎን ለጎን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባ ወይዘሮ አዜብ አስገንዝበዋል።