ቀጥታ፡

የዘንድሮው የመስቀል በዓል ሁለት የነበረው ሲኖዶስ አንድ በመሆን የሚከበር በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል-ምዕመናን

አዲስ አበባ መስከረም 17/2011 ላለፉት 26 ዓመታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን በሁለት የተከፈሉ ሲኖዶሶች ነበሯት፤ ውጭ የሚገኘውና የሀገር ውስጡ በሚል። ሁለቱም ሲኖዶሶች በያሉበት ሆነው ምዕመኑን ሲመሩ ቆይተዋል፤ ይሁን እንጂ እዚህ ግባ በማይባል ልዩነት በአንድ ቤተ-ክርስቲያን ሁለት አስተዳደር መኖሩ በምዕመኑ ዘንድም ቅሬታን አስከትሎ ቆይቷል። በቅርቡ ግን በሲኖዶሶቹ መካከል እርቀ-ሰላም ወርዶ በብጹዕ ወ ቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ የሚመራው ውጭ የነበረው ሲኖዶስ  ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ አገር በመግባት አንድነትን ፈጥሯል። በዘንድሮው የደመራ በዓልም በዓሉ ላይ ብጹዕ ወ ቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ እና ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ በአንድ መንበር ተቀምጠው ምዕመኑን ባርከዋል። ሁለቱ ሲኖዶሶች ወደ አንድነት መጥተው ፓትርያርኮቹም በአንድ መንበር ተቀምጠው የመስቀል በዓል ሲከበር የመጀመሪያው ነው። የመስቀል ደመራ በዓልን በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የታደሙ ምዕመናንም ሁለቱ ሲኖዶሶች አንድ ሆነው የተከበረ በዓል በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።  በቤተክርስቲያናችን አንድነትና ፍቅር ግድ ስለሆነ ሲኖዶሶቹ ደግሞ ታርቀው እዚህ ቦታ ላይ አንድነት ሲኖራቸው ነው ያለው አቤኔዘር  ብዙአየሁ ፡፡  ሊቀ-ትጉሃን ታደሰ ጋሞ ለኔ ብቻ ሳይሆን ህዝቡም ትልቅ ሞራል ተሰምቶታል። ሁለቱ ሲኖዶሶች ተከፋፍለው የነበረው ወደ አንድነት መጥተው በኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ሲኖዶስ መመራቱ በጣም ደስታ እንዳለው ተናግሯል  የደመራ በዓል በአዲስ አበባ የከተማዋ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ሊቃውንት ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ሌሎችም የበዓሉ ታዳሚዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።                                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም